አቡነ ጳውሎስ በጠና ታመው ሆስፒታል ገብተዋል

(Aug. 15) አቡነ ጳውሎስ በጠና ታመው ሆስፒታል መግባታቸውን በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ዙሪያ የሚያጠነጥኑ  ዜናዎችን በቅርበት በመዘገብ የሚታወቀው ደጀ ሰላም ድረ-ገጽ ዘገበ። ከፓርያሪክ ረዳቶች አንዱ የሆኑትን አባ እንቁ ባህርይ ግን፤ “የለም አልታመሙም እሳቸው ቤት ነው ያሉት” ብለዋል።

አባ ጳውሎስ ትናንት ምሽት በጠና ታመው ባፋጣኝ ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል እንደተወሰዱ የሚያትተው ይኸው ዜና ዘገባ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ራሳቸውን ችለው መራመድ አቅቷቸው መኪናቸው ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ እንኳን ከግራና ከቀኝ ሌሎች ሰዎች እየደገፏቸው እንደነበር አብራርቷል።

የተያዘውን የፍልሰታ-ለማሪያም ጾም በመንበር ፓትርያርክ ቅድሰተ ቅዱሳን ማሪያም ገዳም ጸሎተ ቅዳሴ ላይ እንደነበሩ የተናገሩት እነዚሁ የደጀ-ሰላም ምንጮች፤ ምንም እንኳን የአባ ጳውሎስን አጣዳፊ ህመም ምንነት ለይተው ባይገልጹም የጤንነታቸው ሁኔታ አስጊ በመሆኑ በሆስፒታሉ ሃኪሞች ከፍተኛ ክትትል ስር መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አባ ጳውሎስ የጤናቸው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በተለይም ከጉልበታቸው በታች የሚገኘው የእግራቸው ክፍል መጎዳቱን ዘግቦ የነበረው ይኸው ድረ-ገጽ፤ በዚህም የተነሳ ጤናቸውን ለመከታተል የሚያደርጉት ሳምንታዊ ወጪ ከስድሳ ሺህ ብር በላይ ማሻቀቡን ጠቁሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢሳት ያነጋገራቸው ከአባ ጳውሎስ ረዳቶች አንዱ አባ እንቁ ባህርይ ባልቻ ሆስፒታል ሰው ሊጠይቁ መሄዳቸውን፤ እሳቸው ግን አለመታመማቸውን ገልጸዋል።

አባ ጳውሎስ በቅርቡ 20ኛ ዓመት በዓለ ሲመታቸውን መጀመሪያ በቤተ ክህነት በማስከተል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በተጋበዙበት በሸራተን አዲስ ሆቴል፤ እንዲሁም ለሶስተኛ ጊዜ በክራውን ሆቴል በወኪሎቻቸው አማካኝነት ከፍተኛ ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ድል ያለ ድግስ አዘጋጅተው ግብር ማብላታቸው መዘገቡ ይታወሳል።

ቤተክርስቲያኗ፤ በተለይም የዋልድባ ጥንታዊ ገዳም እና በውስጡ የሚገኙት መነኮሳት ህልውና እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰበት ባሁኑ ወቅት፤ እርሳቸው እንደ ቤተክርስቲያኗ አባትነታቸው ከመነኮሳቱና ከምእመናኑ ጎን በመቆም፤ ይህንን መቃወም ሲጠበቅባቸው በተቃራኒው የመንግስትን አቋም በግልጽ ያራምዳሉ በሚል፤ የሚወቅሱዋቸው ቁጥራቸው እየበዛ ነው።

አቡነ ጳውሎስ ለማነጋገር እንችል ዘንድ ስልካቸውን ከረዳታቸው አባ እንቁ ባህርይ ለመቀበል ያቀረብነው ጥያቄ ባለመሳካቱ፤ ባልቻ ሆስፒታል ወይንም ቤታቸው እንዳሉ ለማረጋገጥ አልቻልንም።

ሆኖም የኢሳትም ሌሎች ምንጮችም አቡነ ጳውሎስ መታመማቸውን አረጋግጠዋል።