ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ተመላሽ ያላደረጉ ድርጅቶችን መለየቱ ታወቀ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 17/2011)ለገቢና ለወጭ ንግድ አገልግሎት በሚሊየን የሚቆጠር ዶላር ወስደውና ምርቶች ወደ ውጪ ልከው ገንዘቡን ወደ ሀገርቤት ያልመለሱ 240 ድርጅቶችን ብሔራዊ ባንክ መለየቱን አስታወቀ።

ባለፉት አስራ አራት ዓመታት በርካታ አስመጪዎች የተለያዩ ምርቶችን እንዲያስመጡ ከተለያዩ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ ተፈቅዶላቸው ነበር።

ነገር ግን ምርቱን ሳያስመጡ እንዲሁም ምርት ልከው ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬን ሀገር ውስጥ ሳያስገቡ በመንግስት በተደረገ ጫና ከብሄራዊ ባንክ እገዳቸው ተነስቶላቸው ተጨማሪ ምንዛሪ መውሰዳቸውን ዋዜማ ሬዲዮ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ህግ መሰረት የትኛውም አስመጪ ከየትኛውም ንግድ ባንክ በተፈቀደለት የውጭ ምንዛሪ ተመጣጣኝ ምርት ማስገባት ይኖርበታል።

በዚህ ህግ መሰረት በወሰደው የውጭ ምንዛሪ ተመጣጣኝ ምርት ካላስገባ በድጋሚ ምንም አይነት ምንዛሬ አይፈቀድለትም ፣ ምርት መላክም አይችልም።

ብሔራዊ ባንክም እንዲህ አይነት ችግር የተገኘባቸው ነጋዴዎች ምንዛሬን ከየትኛውም ባንክ እንዳያገኙ የማድረግ ስልጣን እንዳለውም ነው የተነገረው።

የዋዜማ ራዲዮ ዘገባ እንደሚያመለከተው ይህን አሰራር በጣሰ መልኩ በርካታ ነጋዴዎች እንደልብ የውጭ ምንዛሬ ሲፈቀድላቸው ቆይቷል።

በዘገባው እንደተመለከተው ከባለስልጣናት ጋር በነበራቸው የጥቅም ትስስር እና የልማት ፕሮጀክቶችን ከለላ በማድረግ እንዲሁም በሃገሪቱ በአቅርቦት ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት በሚደረግ ጥረት የመፍትሄ አካል ሆነው በመቅረብ ከባንኮች ያለገደብ ምንዛሪ ሲወስዱ የነበሩ ድርጅቶች በርካታ ናቸው።

በዚህ ድርጊት ውስጥ የ240 አስመጪና ላኪዎች ዝርዝር መታወቁም ነው የተገለጸው።

ዋርካ ትሬዲንግ የተባለ ሰሊጥ ላኪ ኩባንያ እና አብዱል ሰመድ ቡና ላኪ ምርቶችን በላኩ ቁጥር በትንሹ ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሀገር ውስጥ የማያመጡ መሆናቸው ታውቋል።

በመስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ፣ መሰቦ ቢውልዲንግ ማቴሪያል ፣ አስገዶም አብርሀ እና ኤዜድ ፒኤልሲ እንዲሁም ጎላጎል ትሬዲንግ ብረትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በተለያየ ጊዜ ለማምጣት ምንዛሬ ተፈቅዶላቸው ነገር ግን ምርቶቹን  መምጣታቸው ሳይረጋገጥ እንደገና የውጭ ምንዛሬ ተጠቃሚ ሆነዋል።

አይካ አዲስና ኢቱር የተባሉት የጨርቃጨርቅ ኩባንያዎች ደግሞ ጥሬ እቃ ለማምጣትና ምርት ሲልኩም ምንዛሬ ማስቀረታቸው በዝርዝሩ ላይ ተጠቅሷል።

ሆኖም ሁሉም ኩባንያዎች ለዚህ ተግባራቸው ተመጣጣኝ ርምጃ አልተወሰደባቸወም።

ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት እስከ አስራ አንድ ቢሊየን ዶላር ህጋዊ ባልሆነ መልኩ ከሀገር ወጥቶ እንዲሸሽ የተደረገባት ሀገር መሆኗን አለማቀፍ የፋይናንስ ወንጀሎች ጥናቶች ያመለክታሉ።