በብሪታኒያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሞት እየጨመረ ነው ተባለ

          (ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 12/2011) በብሪታኒያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ሞት ባለፉት 5 አመታት እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ።

          ባለፈውአመት ብቻ 600 ያህል የጎዳና ተዳዳሪዎች በእንግሊዝና በዌልስ ግዛት መሞታቸውን የብሪታኒያ መንግስት መረጃዎች አመልክተዋል።

          ባለፉት ሁለት አመታት የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ሞት በ24 በመቶ መጨመሩም ታውቋል።

          እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ የጎዳና ተዳዳሪዎቹ ቁጥር በ169 በመቶ መጨመሩን የግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በመጥቀስ ሮይተርስ ዘገባውን አቅርቧል።

ይፋዊ የመንግስት መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ደግሞ አልጀዚራ ባቀረበው ዘገባ ከሞቱት 600 ያህል የጎዳና ተዳዳሪዎች 84 በመቶው ወንዶች መሆናቸውን አመልክቷል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2014 በእንግሊዝና ዌልስ ግዛት የሞቱት የጎዳና ተዳዳሪዎች 475 ሲሆኑ በ2017 ይህ ቁጥር ወደ 597 አሻቅቧል።

በ2017 ከሞቱት የጎዳና ተዳዳሪዎች ውስጥ 503ቱ ወንዶች ሲሆኑ የሴቶች ቁጥር 94 እንደሆነም የብሪታኒያ ብሔራዊ ስታስቲክስ መስሪያ ቤት ይፋ ካደረገው ሪፖርት መመልከት ተችሏል።

ከ597ቱ ሟች ጎዳና ተዳዳሪዎች ውስጥ 250 የሚሆኑት በአደጋ ሲሞቱ 78ቱ ራሳቸውን አጥፍተዋል።

በጉበት እንዲሁም በመተንፈሻ አካል ህመሞችና በመሳሰሉት የሞቱ መኖራቸውም ተመዝግቧል።

ለህልፈት የዳረጋቸው ህመም በዋናነት ከእጽና አልኮል ጋር የተያያዙ መሆኑም በሪፖርቱ በዝርዝር ተቀምጧል።

ከአጠቃላዩ ሟቾች 136ቱ ወይንም 15 ነጥብ 4 በመቶው ለንደን ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

በአሁኑ ወቅት በብሪታኒያ 320 ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎች መኖራቸውን ሃውሲንግ ቻሪቲ ሼልተር የተባለ ተቋም ሪፖርት ያሳያል።