አቶ ፍጹም አረጋ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ተሾሙ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 15/2011)በአሜሪካ ዋሽንግተን የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ በቆዩት በአቶ ካሳ ተክለብርሃን ምትክ አቶ ፍጹም አረጋ መሾማቸውን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።

እንዲሁም ለ27 ዓመታት በሕዉሃት ሰዎች ብቻ በርስትነት ተይዞ በቆየው ቻይና ደግሞ አቶ ተሾመ ቶጋ በአምባሳደርነት መሾማቸውም ተመልክቷል።

በአጠቃላይ 59 ያህል ዲፕሎማቶች በተለያዩ ሃገሮች የተመደቡ ሲሆን የእነዚህ ዝርዝር በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።

ቀደም ሲል ከተመደቡት 59 ሰዎች ውስጥ በሰብዓዊ መብት ረገጣና በሌብነት ወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦች ስለተገኙበት ዝርዝሩ መከለሱን የሚገልጹት ምንጮች የተጣራው ዝርዝር ይፋ እንደሚሆንም አመልክተዋል።

የሕወሃት አገዛዝ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የሜቴክ ሃላፊዎችን የሌብነት ወንጀል በይፋ በደብዳቤ በማጋለጥ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የጻፉት የጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ሱሌይማን ደደፎ በአዲሱ ድልድል ኳታር መመደባቸውም ለማወቅ ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በውጭ አገራት ኢትዮጵያን ለሚወክሉ አምባሳደሮች ሹመት መስጠታቸው ተሰምቷል።