የማዳበሪያ አምራቹ ያራ ለባለስልጣናት ጉቦ ይሰጣል ተባለ

(Aug. 15) በኖርዌይ የሚታተመውና ከፍተኛ ተነባቢነት ካላቸው ጋዜጦች አንዱ የሆነው አፍተንፓስት የተሰኘው  ጋዜጣ በቅርቡ ባወጣው የምርመራ ዘገባ፤ ያራ በመባል የሚታወቀው የማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ለኢትዮጲያ መንግስት ከትርፍ 30 ፐርሰንት ለማካፈል መዋዋሉን አጋለጠ።

ሂውማን ራይትስ-ዎች ማዳበሪያን ገዢው ፓርቲ እንደ ስልጣን ማስፈጸሚያ መሳሪያ እንደሚጠቀምበት አጋልጦ እንደነበር ያተተው ይኸው ጋዜጣ፤ በቅርቡ ኢትዮፓስት በሚባል የማዳበሪያ ኩባንያ ስም የተፈጸመው ስምምነት አምባገነናዊውን ስርአት እንደማጠናከር ይቆጠራል ሲል አፍተን ፓስት ተችቷል።

በምርጫ 97 ማግስት ያራ ኩባንያ ለአቶ መለስ ዜናዊ ያረንጓዴ አብዮት ሽልማት በመስጠቱ ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የነበረ ሲሆን፤ ከዚያ ጊዜ በሁዋላ  ያራ በኢትዮጲያ የማዳበሪያ አቅራቢ ለመሆን መብቃቱ ይታወቃል።

አፍተንፖስት ያነጋገራቸው ሻን ኢጌላንድ የተባሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች፤ ያራ የፈፀመውን ውል አውግዘው ኖርዌይም ሆነች ኩባንያው ከአምባገነኖች ጋር መፋቀር እንደማያዋጣቸው ተናግረዋል።