ቴዲ አፍሮ ለመጪው አዲስ አመት የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባል

ነሀሴ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዝነኛው ኢትዮጵያዊ አቀንቃኝ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ለመጪው 2005 የኢትዮጽያዊያን አዲስ አመት ዋዜማ
ከአዲካ ኮሚውኒኬሽን ኤንድ ኢቬንትስ ጋር በመተባበር የሙዚቃ ዝግጅቱን በግዮን ሆቴል እንደሚያቀርብ ተገለፀ፡፡
በቅርቡ የወጣውን ጥቁር ሰው የተባለውን አልበሙን አስመልክቶ በሚደረገው በዚህ የሙዚቃ ዝግጅት ላይ ከ15 ሺ
በላይ የቴዲ አድናቂዎች ይታደማሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ ይህ ጥቁር ሰው ተብሎ የሚጠራው አልበሙ ለህዝብ ከቀረበ
በኁላ አዲስ አበባ ውስጥ የሚያቀርበው የመጀመሪያው የሙዚቃ ዝግጅቱ ነው፡ የትኬት ሽያጭ ነሀሴ 14 ቀን 2004
ዓ.ም እንደሚጀምር ይፋ ተደርጓል።

አቡጊዳ በሚል ስያሜው ከሚታወቀው የሙዚቃ ባንድ ጋር በመሆን ቴዲ አፍሮ በልዩ ሁኔታ ባጌጠ መድረክ ላይ የሙዚቃ አፍቃሪዎችን ሲያዝናና ያመሻል፡፡  የሙዚቃ ዝግጅቱን አስመልክቶ ቴዲ አፍሮ እና የአዲካ ኮሚውኒኬሽን ኤንድ ኢቬንትስ ተወካዮች በቅርቡ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡም ተገልጹል፡፡ ቴዲ አፍሮ እና የአቀንቃኙን የመጨረሻ የሙዚቃ አልበም ለህዝብ ያቀረበው የጥበብ አጋሩ
አዲካ በመካከላቸው ያለው አንድነት አሁንም ጠንክሮ እንደሚቀጥል እና ከዚህም ባሻገር አብረው መስራታቸውን
እንደማያቁርጡ አስታውቀዋል፡፡

ከተወዳጁ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር ተቆራኝቶ የሚጠራው ቴዲ አፍሮ ከስሙ ጋር ተያይዘው የሚነሱ አራት የሙዚቃ
አልበሞች አሉት፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለያዩ የዓለም ከተሞች በመዘዋወር ቁጥራቸው በዛ ያሉ አድናቂዎቹ በተገኙበት
የሙዚቃ ዝግጅቱን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በቅርቡ በለንደን ከተማ የኦሎምፒክ ውድድርን አስመልክቶ የተዘጋጀውና
በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀውም ኮንሰርት ከእነዚሁ ዝግጅቶች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ ጥቁር ሰው የተሰኘው አልበሙ
ወደሁላ ትተን የመጣነውን አስገራሚውን የኢትዮጵያን ታሪክ ሲያስቃኘን ወደፊት ልንወስደው ያሰብነውን እርምጃም
መሰረት ይጠቁመናል፡፡ በዚህ ስራው ቴዲ አፍሮ ለብዙ አመት ሲነገር የቆየን ታሪክ ህይወት ዘርቶበት እንደታየ
አዲካ ኮሙኒኬሸን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide