ማኅበረ ቅዱሳን በአክራሪነት መፈረጅ ቤተ ክርስቲያንን እንደ መፈረጅ ነው ተባለ

ነሀሴ ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-“ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶ ያዋቀረውን ማኅበረ ቅዱሳን በአክራሪነት መፈረጅ ቤተ ክርስቲያንን እንደመፈረጅ ነው” ሲሉ የጅማ ሀገረ-ስብከት  ሊቀ-ጳጳስ ተናገሩ።

ብጹዕ አቡነ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ይህን ያሉት፤   የጅማ ሀገረ ስብከት ጠቅላላ ጉባኤ ሰሞኑን  የ2004 ዓ.ም. ዕቅድና ክንውንን ለመገምገም እና የ2005 ዓ.ም. ዕቅድን ይፋ ለማድግ በጠራው ስብሰባ ላይ ነው።

የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ማህበረ-ቅዱሳንን በተደጋጋሚ ፦” በአክራሪነት”ሲወነጅሉ ይደመጣሉ።

ጉባኤውን የመሩት የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ጠቅላላ ጉባኤው የ2004 ዓ.ም. የሥራ ግምገማ ማድረጉ ካለፈው ተሞክሮ በመውሰድ ለቀጣይ የተሻለ ለመሥራትና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ለማሻሻል የሚረዳ በመሆኑ በቀጣይም የተሳካ ሥራን ለመሥራት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ስለሺ አስፋው ከ2004 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በተጨማሪ ሀገረ ስብከቱ የተዘጉ አብያተ ክርስቲያናትን ለማስከፈት ይረዳ ዘንድ እየተሠራ ያለው ባለ 5 ፎቅ ሕንፃ ግንባታን በተመለከተ የሒሳብ ራፖርት አቅርበዋል፡፡ ለዚህ ሥራም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አድባራትና ግለሰቦችን አመሰግነዋል፡፡

በጉባኤው ማጠቃለያ ላይም ብፁዕነታቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ በአንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ቅዱስ ሲኖዶስ ሕግ አውጥቶ ያዋቀረውን ማኅበረ ቅዱሳንን በአክራሪነት ስም መፈረጅ፤ ቤተ ክርስቲያንን እንደመፈረጅ በመሆኑ ይህን የሚያደርጉ አንዳንድ አካላት ከድርጊታቸው መታረም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም በሀገረ ስብከቱ በበጀት ዓመቱ ብልጫ ሥራ የሠሩ አካላት የተሸለሙ ሲሆን፤ የማኅበረ ቅዱሳን የጅማ ማእከል የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በምርጫ 97 ኢህአዴግ  ድምጽ ለማጣቱ አንድኛው ተጠያቂ ማህበረ-ቅዱሳን እንደሆነ የቆጠሩት  የአቅም ግንባታ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ፤ ያን ቅሬታቸውን በማስታከክ የ ኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንን፦”የነፍጠኞች ዋሻ ብለው መዝለፋቸው አይዘነጋም።

ባለፈው ዓመት ደግሞ የስኳር ኮርፖሬሽን ሚኒስትሩ እና የ ህወሀቱ መስራች አቶ ስብሀት ነጋ ለማህበረ-ቅዱሳን አመራር ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ይታወሳል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide