በሳዑዲ-አረቢያ 35 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ተጠርዘው ከአገር ተባረሩ

ሐምሌ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የሳዑዲ አረቢያ መንግስት ከ7ወራት በላይ በእስር ቤት ሲያሰቃያቸው የነበሩ 35 ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችን ባሳለፍነው ሳምንት ከአገሪቱ ማባረሩ ተገለፀ።

እነዚሁ ኢትዮጵያውያን ተይዘው የታሰሩት፣ ባለፈው ታህሳስ 5 ቀን 2004 ዓ.ም በጅዳ ከተማ በአንደኛው ጓደኛቸው ቤት ተሰባስበው በመፀለይ ላይ ሳሉ ሲሆን፣ በእስር ላይ ሳሉ ሃይማኖታቸውን በግዴታ እንዲቀይሩ ከፍተኛ ማስፈራሪያና ጫና ይደረግባቸው እንደነበር ዓለም አቀፍ የክርስቲያኖች ድርጅት አስታውቋል።

ከነዚሁ ኢትዮጵያውያን መካከል 26ቱ ሴቶች ስድስቱ ደግሞ ወንዶች ሲሆኑ፤ በአሜሪካ መንግስት ዓለም አቀፍ የሃይማኖቶች ነፃነት ኮሚሽን፣ እንዲሁም የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተጨማሪ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያውያኑ በእስር ቤት ሳሉ፣ የወሲብ ጥቃትና በአካላቸው ላይ በግልጽ የሚታይ ድብደባ ተፈጽሞባቸዋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ካሁን ቀደም በእስረኞቹ ላይ እየደረሰባቸው የነበረውን ጥቃት በመቃወም ባወጣው መግለጫ እንደጠቆመው ሴቶች በብልታቸው ውስጥየደበቁት ነገር ይኖራል በማለት በአንድ ጓንት ሁሉንም ሲመረምሩ እንደነበር አስታውቆ ነበር።

ሳኡዲ አረቢያ እ.ኤ.አ. ከ2004 ጀምሮ የሃይማኖት ነፃነት የተረጋገጠባት አገር ተብላ በአሜሪካ መንግስት ጭምር እውቅና የተሰጣት አገር ብትሆንም፣ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ባልሆኑ በውጭ አገር ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ጭቆናና በደል ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ እያወጡት ካለው ማስረጃ ማረጋገጥ ይቻላል።

የሳዑዲ መንግስት እ.ኤ.አ በ2006 ላይ ከእስልምና በቀር የማንኛውም ሃይማኖት ተከታይ በአገሪቱ ውስጥ በይፋ አምልኮ እንዳይፈጽም የሚያግድ ሕግ ቢያወጣም፣የሌላ እምነት ተከታዮች በየመኖሪያቸው የራሳቸውን አምልኮ እንዲፈጽሙ ፈቅዶ ነበር።

የዓለም አቀፉ የክርስቲያኖች ድርጅት የሕግና የፍትህ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት  ጆርዳን ሲኩሎው ይህንኑ አስመልክቶ ለኢየሩሳሌም ፖስት ድረ-ገጽ እንደገለፁት “በኢትዪጵያውያኖቹ ላይ የተፈፀመው ጥቃት፣ በሳኡዲ አረቢያ ውስጥ የእስልምና ዕምነት ተከታይ ያልሆኑ ሰዎች በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ የራሳቸውን አምልኮ መፈፀም እንደማይችሉ ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቷ ላይ ምንም አይነት የሃይማኖት ነፃነት እንደሌለ የሚያረጋግጥ ክስተት ነው ብለዋል።“

ከእስረኞቹ መካከል አንደኛውም፣ ዓለም ዓቀፍ የክርስቲያኖች ድርጅት ባደረገው ብርቱ ጥረትና ግፊት ተለቀው በሰላም ወዳገራቸው በመግባታቸው እንደተደሰቱ ገልጿል።ይኸው ለክርስቲያኖች መብት የቆመው ድርጅት ልዩ ልዩ አካላትን በማስተባበር እ.ኤ.አ ማርች 26 2012 ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የሳውዲ አረቢያኤምባሲ ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ፣ ያለአግባብ የታሰሩት ኢትዮጵያውያን እንዲፈቱ ለንጉስ አብዱላህ ጥያቄ አቅርቦ ነበር።  ባንፃሩ የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን እስረኞች ከነበሩበት የስቃይ ህይወት ለማላቀቅ ጥረት ማድረግ ትቶ “በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳኡዲ አረቢያ የገቡ ናቸው” በማለት የዜጎችን መብት ለማስከበር በቅድሚያ መቆም ሲገባው፣ በተቃራኒው ለመሳለቅ መሞከሩ ብዙዎችን ያሳዘነና ያሸማቀቀ ምላሽ ነበር ሲል ቅዱስ ሀብት በላቸው ከአውስትራሊያ ዘግቧል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide