የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በዕፅ ማዘዋወር ተይዘው ስለተቀጡት ዲፕሎማት የማውቀው ነገር የለም አለ

ሐምሌ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በለንደን- ሔትሮ አውሮፕላን ማረፊያ 56 ኪሎ ግራም ካናቢስ ሲያዘዋውሩ ስለተያዙት ኢትዮጵያዊት ዲፕሎማት ጉዳይ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር  ምንም አላውቅም አለ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቪዛ ክፍል ውስጥ ሠራተኛ የነበሩት ወይዘሮ አመለወርቅ ወንድማገኝ 160 ሺሕ ፓውንድ ዋጋ ያለው የካናቢስ ዕፅ ሲያዘዋውሩ ተይዘው፣ ባለፈው ሳምንት የ 33 ወር እስራት እንደተፈረደባቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ስለድርጊቱ መስማታቸውን እና ጉዳዩን ገና እያጣሩ መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል።

“በጉዳዩ ዙሪያ ለጊዜው ከዚህ በላይ ስመናገር አይቻልም”ሲሉም አክለዋል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ።

ከዓመት በፊት የ ኢትዮጵያ  አውሮፕላን ለደቡብ ሱዳን ተዋጊዎች መሳሪያ አጓጉዟል የሚሉ ዘገባዎችን ተከትሎ የሱዳን የደህንነት ሠራተኞች በደቡብ ሱዳን  በሚገኝ አንድ የኢትዮጵያ ኮሎኔል ቤት ባደረጉት ድንገተኛ ፍተሻ በ አገሪቱ ህግ የተከለከሉ የአልኮል መጠጦችን  እንደገኙ መገለጹ ይታወሳል።

በዲፕሎማትነትም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ሥራዎች በውጪ አገራት የሚመደቡ ኢትዮጵያውያን፤ ከተወከሉበት ተግባር ይልቅ የግል ጥቅም ለማጋበስ በመሯሯጥ ይወቀሳሉ።

የ36 ዓመቷ ወይዘሮ አመለወርቅ  በምዕራብ ለንደን ፍርድ ቤት ሲጠየቁ ፤56 ኪሎ ግራሙን ካናቢስ ከአዲስ አበባ አየር መንገድ ሲነሱ ከሰው የተቀበሉት መሆኑን በመጥቀስ፤  ዕቃውን የተቀበሉት  ግን ሥጋና በርበሬ ነው የሚል እምነት እንደነበር  ተናግረዋል፡፡

ያቀረቡትን መከላከያ ምላሽ ያልተቀበለው  ፍርድ ቤትም፤ የወይዘሮ አመለወርቅን የዲፕሎማቲክ መብት በመግፈፍ በዕፅ በማዘዋወር ወንጀል የሁለት ዓመት ከዘጠኝ ወር እስራት ፈርዶባቸዋል፡፡

ወይዘሮ አመለወርቅ ስለዕፁ ሲጠየቁ የተለያዩ ውሸቶችን እንደተናገሩ የገለጹት ዳኛው፦ “ግለሰቧ አፈጮሌ ናት” ሲሉ  ኢትዮጵያዊቷን ዲፕሎማት ዘልፈዋቸዋል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide