በሜልበርን ኢትዮጵያዊያን ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ

ሐምሌ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዘር ቋንቋና ሃይማኖት ያለየው በሜልበርን የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ኢህአዴግ መራሹ መንግስት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ እየፈጸመ ያለው ኢ.ሰባዊና ኢ.ፍትሃዊ ተግባር እንዳስቆጣው ቅዳሜ ኦገስት 4 ቀን ባደረገው ከፍተኛ የተቃውሞ ሰልፍ ገለጸ።

በመቶዎች የሚቆጠረው ኢትዮጵያዊ በሜልበርን ፓርላሜንት ፊት ለፊት በመገኘት ተቃውሞውን ማሰማት የጀመረው ከረፋዱ 4 ሰአት ጀምሮ ነበር።

በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ በሜልበርን የምስራቅ አፍሪካ ሙስሊም ማህበረሰብ ተወካይና የቢላል ኢትዮጵያዊያን ማህበር ተወካይ የሰልፉን አላማ አስመልክተው ንግግር ያደረጉ ሲሆን ኪኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክያንም በህጋዊ ሲኖዶስ የአውስትራሊያ የአውሮፓና የአፍሪካ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹ አቡነ መቃሪዎስ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ በሙስሊም ወገናችን ላይ እየተፈጸመ ያለውን በደል በጽኑ እንደምትቃወም ገልጸዋል።

የቢላል ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ማህበረሰብ ተወካይ በሙስሊም ኢትዮጵያዊ ወገን ላይ እየደረሰ ያለውን በደልና ግፍ በመቃወም ሃይማኖት ዘርና ቋንቋ ሳይለይ በሰልፉ ላይ የተገኘውን ኢትዮጵያዊ አመስግነው፤ በሃይለስላሴና በደርግ ስርአት ያልነበረው የኃይማኖት ጣልቃ ገብነት በኢሃዴግ እየተፈጸመ ነው ብለዋል። የቢላል ተወካይ ቀጥለውም ” ሃገር የጋራ ሃይማኖት የግል የሚለው መመሪያ ዛሬ በኢሃዴግ መንግስት ሃገርም ሃይማኖትም የመንግስት በሚል ተለውጧል በማለት በመንግስት እየተፈጸመ ያለውን የሃይማኖት  ጣልቃ ቀብነት አመላክተዋል።

በሜልበርን የምስራቅ አፍሪካ ሙስሊም ማህበረሰብ ተወካይ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ነብዩ ማህመድ የሰው መብት የሚከበርባት ሃገር ብለው ለስደተኞቹ ሙስሊሞች የመረጡላቸው ኢትዮጵያ እንደነበር አስታውሰው ይህ ቀና ስምና ክብር ዛሬ በኢህአዴግ መንግስት ተገሷል ብልዋል፡፤

ቀጥለው ለሰልፈኛው ኢትዮጵያዊ ንግግር ያደረጉት የአውስትራሊያ የአውሮፓና የአፍሪካ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብጹ አቡነ መቃሪዎስ ሲሆኑ አቡነ መቃሪዎስ በንግግራቸው የኢሃዴግ መንግስት የዘር ፖለቲካ ከዚህ በኋላ እንደማይሰራና ዛሬም ነገም አንድ ሆነን መቆም እንደሚገባን አበክረው መክረዋል፡፤

አቡነ መቃሪዎስ በሜልበርን የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በቅርቡ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ በተመሳሳይ የህብረት ተቃውሞ በማድረጋቸው ያስገኙትን  ውጤት አስታውሰው አድናቆታቸውን ገልጽዋል። በመጨረሻም እነሱ ይሞታሉ ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም ትኖራለች በማለት ንግግራቸውን አሳርገዋል።

በሰላማዊ ሰልፉ የተገኘው ከሁሉም ብሄር የተውጣጣው ኢትዮጵያዊ በ እንግሊዘኛ በአማርኛ በኦሮሞኛ የተጻፉ ልዩ ልዩ መፈክሮችን አንግቦ በድምጽም የተለያዩ መፈክሮችን ሲያሰማ አርፍዷል።

ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፈኛው ከያዛቸው መፍክሮች መካከል

  • የመጅሊስ ምርጫ በመስኪድ እንጂ በቀበሌ አይሆንም
  • የታሰሩት መፍትሄ አፈላላጊ ወኪሎቻችን ይፈቱ
  • በሃይማኖት ጣልቃ መግባት ይቁም
  • የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ይፈቱ
  • መብትን መጠየቅ አክራሪነት አይደለም

የሚሉት ጥቂቶቹ ሲሆኑ ሰልፈኛው በዚሁ መልክ ተቃውሞውን ሲገልጽ ከቆየ በኋላ  በታቀደው መሰረት መልዕክቱን አስተላልፎ የሰልፉ ፍጻሜ ሆኗል።

ይህ ሰልፍ የኢትዮጵያ  ትክክለኛ ገጽታ የተንጸባረቀበት የህብረ ብሄር አገርንቷ የታየበት ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩ የተለያዩ ሃይማኖቶች የሚከተሉ ህዝቦች የጋራ መጠለያ እንደሆነች ያረጋገጠ ነበር በማለት የኢሳት ተባባሪ ሪፖርተር የሆነው ሳምሶን አስፋው ከሜልበርን ዘግቧል።

____________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide