አትሌት ቲኪ ገላና የኦሎምፒክ ክብረ-ወሰን ሰበረች

ሐምሌ ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የበለንደን ኦሎምፒክ የሴቶች ማራቶን ውድድር በአትሌት ተኪ ገላና የተወከለችው ኢትዮጵያ  የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ሆነች።

ኢትዮጵያ በ ኦሎምፒክ የሴቶች ማራቶን  ለመጀመሪያ ጊዜ ያሸነፈችው፤ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ 1996 ዓመተ ምህረት  አትላንታ ላይ በተካሄደው የኦሎምፒክ ውድድር በፋጡማ ሮባ አማካይነት ነው።

በጠይሟ እንስት አንበሳ በቲኪ ገላና የተገኘው የለንደኑ ማራቶን ውጤት፤ ኢትዮጵያ ከ 16 ዓመት በሁዋላ በኦሎምፒክ ማራቶን  ያስመዘገበችው ሁለተኛ ድል ሆኖ ተነዝግቧል።

41 ኪሎ ሜትሩን ዘና ብላ በመሮጥ ወድድሩን ሲያስተላልፉ የነበሩትን ኮሜንታተሮች ያስደነቀችው አትሌት ቲኪ፤ እየተፈራረቁ ሲያደክሟት የነበሩትን ኬንያውያን አትሌቶች ታክቲክ በጽናት ተቋቁማ ወደ ፊት ከገፋች በሁዋላ፤ በመዳረሻው ላይ ጥርሶቿን ነክሳ ባለ ሀይሏ በመሮጥ  የአሸናፊነቱን ገመድ በጥሳለች።

ቲኪ ገላና ሩጫውን ያጠናቀቀችው  በ2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ  ከሰባት ሰከንድ ሲሆን፤ይህም  በሴቶች የኦሎምፒክ ማራቶን አዲስ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።

በውድድሩ  አትሌት ቲኪን እስከመጨረሻው ሲፎካከሯት የነበሩት የኬንያ እና የሩሲያ አትሌቶች ሁለተኛ እና ሦስተኛ ወጥተዋል።

በማራቶኑ ከቲኪ ጋር ኢትዮጵያን ወክለው  የሮጡት ማሬ ዲባባና አሰለፈች መርጊያ  እንደ ቅደም ተከተላቸው 23ኛና 42ኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።

በጥሩነሽ ዲባባ  የተሟሸው የለንደን ኦሎምፒክ ድል በቲኪ ገላናን መደገሙን  ተከትሎ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ፤ በፌስ ቡክ.በትዊተርና በመሰል ማህበራዊ መገናኛዎች ደስታቸውን አየገለፁ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አትሌቲከስ ቡድን የማራቶን አሰልጣኙ አቶ መላኩ ደረሰ  የቲኪን ውጤት ተከትሎ በሰጡት አስተያዬት፦”በወንዶችም ይህን ውጤት ለመድገም በብርቱ እንሰራለን” ብለዋል ።

የኢትዮጵያ የወንዶች የማራቶን ቡድን አባላት  የውድድሩ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በአዲስ በባ ልምምድ እያደረጉ መሆኑንም አሰልጣኙ ተናግረዋል።

የቀድሞው የብሄራዊ አትሌቲክስ ቡድን አሰልጣኝ ዶክተር ወልደመስቀል ኮስትሬ በበኩላቸው፦” በለንደን ኦሎምፒክ በሴቶች ማራቶን ቲኪ ገላና ያስመዘገበቸው ውጤት፤ ያልተጠበቀና አገርን የሚያኮራ ነው” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል።

ቲኪ ገላና አሰልጣኝ ተመድቦላት ስልጠናዋን አጠናክራ ከቀጠለች በሌሎች ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይም ኢትዮጵያን አንደምታኮራ እርግጠና ነኝ ብለዋል-ዶክተር ወልደመስቀል።

_____________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide