ፖለቲከኞች ልዩነታቸውን አስወግደው ወደ ውይይት እንዲመጡ ኢትዮጵያውያን ጠየቁ

ሐምሌ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ፖለቲከኞች እና ዜጎች የአቶ መለስ ዜናውን ህመም ተከትሎ ለኢሳት በሰጡት አስተያየት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ልዩነታቸውን አስወግደው ወደ ውይይት መምጣት ግድ ይላቸዋል ብለዋል።

የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ምክትል ሀላፊ የሆነው ወጣቱ ጸሀፊ ዳንኤል ተፈራ እንደገለጠው ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት ያለው ጉጉት ሊረካ የሚችለው መነጋገር ሲቻል ብቻ ነው ብሎአል።

በዶ/ር ታዲዮስ ቦጋለ የሚመራው መኢአድ የሰሜን ጎንደር ተጠሪ የሆኑት አቶ ያሬድ ግርማ በበኩላቸው ባለፉት 21 አመታት የህወሀት ሰዎች ራሳቸውን ሲያበለጽጉ አገሪቱን ግን አራቁተዋታል። አገርን ለማዳን ከዚህ የተሻለ ጊዜ እንደማይመጣና ሁሉም የፖለቲካ መሪዎች ልዩነታቸውን አስወግደው መንቀሳቀስ አለባቸው ።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች እንደተናገሩት ደግሞ፣ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን በዘርና በሀይማኖት ሳይከፋፈሉ አንድ ግንባር መፍጠር አለባቸው።

በጎንደር ከተማ የሚኖር ሌላ ወጣት በበኩሉ ተቃዋሚዎች ተስፋ የቆረጠውንና ግራ የገባውን ህዝብ ማንቀሳቀስ ይገባቸዋል ብሎአል

ውድ ተመልካቾቻችን በወቅታዊ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ከህዝብ የሰበሰብናቸውን መረጃዎች ሰሞኑን በተከታታይ እናቀርባለን።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide