ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች ችግር መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ መካከል የተወሰኑት ታስረዋል

ሐምሌ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዘጋቢያችን በላከው መረጃ መሰረት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሙስሊም መሪዎችን መታሰር በይፋ ከዘገበ በሁዋላ በርካታ መሪዎች ቤቶች ሲፈተሹ አድረዋል።

ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ መሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ቢሆንም፣ ከጀሚል ያሲን፣ ሼህ ሱልጣን አማን እና የቄራ መስጊድ ምክትል ኡዝታዝ ከሆኑት ሰኢድ አሊ በስተቀር ሌሎችን ፈተዋቸዋል።

በዛሬው እለት ለንባብ የሚበቁት ሰለፍያ እና ሰውቱል እስላሚያ የተባሉት የሙስሊም ጋዜጦች ፣ እንዲሁም አልቁዱስ የተባለው የመጅሊስ ደጋፊ ጋዜጣ ዛሬ ለንባብ ሳይበቁ ቀርተዋል። በዚህም የተነሳ ሆራይዞን ማተሚያ ቤት ከትናንት ምሽት ጀምሮ የታሸገ ሲሆን፣ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰአት ላይ ተከፍቷል። ማተሚያ ቤቱ ታሽጎ በመዋሉ በዛሬው እለት የሚወጡት ሀትሪክና ዘገነርስ ሳይታተሙ ቀርተዋል። የሰለፊያ ጋዜጣ ቢሮ ሌሊት በፖሊስ ተከቦ ሲበረበር እንደነበር ምንጮች ገልጠዋል።

በተያያዘ ዜናም በኢትዮጵያ በሽያጭ ቁጥር መሪ የሆነው ብቸኛው ጠንካራ ጋዜጣ ፍትህ ስለአቶ መለስ የጤና ጉዳይ፣ በአገር ውስጥ፣ በውጭ፣ በተቃዋሚዎች እና በመንግስት ሰዎች ያለውን እሳቤ በመንተራስ ሰፊ ማስረጃና መረጃ በማሰባሰብ ሰፋ ያለ ዜና ሀተታ በፊት ለፊት ገጹ በመያዝ ወደ ማተሚያ ቤት ቢያመራም ሳይታተም ቀርቷል።

ህትመቱ ተጀምሮ ፊልም ተነስቶና 3 ፕሌቶች ተጠናቀው፣ አንድ ፕሌት ብቻ ሲቀር፣ የህትመት ስራውን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች ሀላፊያችን ላሉት አቶ ጌትነት የፊት ገጽ ዘገባውን እንዲመለከት ከሰጡ ዋቸው በሁዋላ፣ ይህ ነገር መቆም አለበት ብለው ሂደቱ እንዲቋረጥ አድርገዋል።

ጠዋት ላይ የተሰባሰቡት የብርሀንና ሰላም ሃላፊዎች የፕሌት እጥረት በመኖሩ ህትመቱ ተቋርጧል የሚል መልስ ለህትመት ክትትል ሀላፊው የገለጡ ሲሆን፣ ማተሚያ ቤቱ ከንግድ ማተሚያ ቤት ወይም ከሆራይዞን ማተሚያ ቤት ፕሌት ተውሶ እንደሚያትም በመግለጥ ለማረጋጋት ሞክሯል። ከዚያም አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ፕሌት አልቆብኛል በማለት ከማክሰኞች በፊት እንደማይታተም ለሀላፊዎች ገልጠዋል።

በእለቱ የፍትህ ጋዜጣ ቢቋረጥም አዲስ ዘመን፣ ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ አል አለም፣ እና በሪሳ ታትመዋል። ቅዳሜና እሁድ ለገበያ የሚቀርቡት በእንግሊዝኛና በአማርኛ የሚታተመው ሪፖርተር፣ ካፒታል፣ ፎርቹን፣ አዲስ አድማስ እና ኢትዮ ቻናል በህትመት ሂደት ላይ ነበሩ።

“ፍትሕ እና የአርብ ሽብሯ” በሚል ርዕስ የጋዜጣው አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ዘግይቶ ባሰራጨው ጽሑፍ

ትላንት ምሽት  የጋዜጣው የሽያጭ ሰራተኛ ብርሃና ሰላም ማተሚያ ቤት ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ተገኝቶ ለ30 ሺህ ኮፒ ህትመት 80፣385 (ሰማኒያ ሺህ ሶስት መቶ ሰማኒያ አምስት) ብር መክፈሉን  በመጥቀስ፤ የፍትህ ህትመት ክትትልም እኩለ ሌሊት ላይ ማተሚያ ቤት ቢደርስም፤ የህትመት ክፍል ሀላፊው ‹‹ፍትህን እንዳታትሙ ተብለናል›› በሚል ጋዜጣዋ ሳትታተም ማደሯን ገልጿል።
በዛሬው ዕለትም የማተሚያ ቤቱን ምክንያት ለማወቅ ወደ ብርሃና ሰላም ከጥቂት ባልደረቦቼ ጋር መሄዱን የጠቀሰው ጋዜጠኛተመስገን፤ እዚያም እንደደረሱ ምክትል ስራ አስኪያጁ -ከሌሎች የድርጅቱ ሀላፊዎች ጋር በመሆን ስብሰባ ቢጤ አድርገው እንዲወያዩ በጠየቋቸው መሰረት መወያየታቸውን አመልክቷል።

“በውይይታችን ምክትል ሥራ አስኪያጁ በፊት ገፅ ላይ ያለ አንድ ዜና ማንሳት እንዳለብን ከመጠቆም ባለፈ እዚህ ጋር የማልገልፀውን እጅግ አሰፋሪ የሆነ መደራደሪያ አቀረቡ፡፡ እኛም የሀገሪቱን ህግ ጠቅሰን ተከራከርን፡፡ ያለስምምነት ከሰዓት 8፡30 ላይ ተወያይተው ውሳኒያቸውን ሊያሳውቁን በቀጠሮ ተለያየን”ብሏል።

ተመስገን በማከልም፦“ቀጠሮውንም ተቀብለን ስንወጣ ከተሰበሰብንበት የም/ስራ አስኪያጁ ትንሿ አዳራሽ በር ላይ የፍትህ ሚንስቴር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እና ዓቃቢ ህግ ተቀምጠው አየናቸው፡፡ በር ላይ ደግሞ በመልክ የምናውቃቸው በርከት ያሉ የፀጥታ ሰራተኞች እንደተለመደው አጀቡን፡፡ ይህንን በዕምሮአችን ይዘን ወደቢሮአችን ተመለስን፡፡ ሰዓቱ እስኪደርስ ለምሳ ወጣን፡፡ ምሳ ለመብላትም ካሳንችስ አካባቢ አንድ ምግብ ቤት ገባን፡፡ ተመግበን ስንወጣም አደባባይ ላይ የመኪናዬ ጎማዎች ፈንድተው አገኘን” ብሏል።

ከዛም ከሰዓት በኋላ በቀጠሯቸው  ሰአት ም/ስራአስኪያጁ ቢሮ ሲደርሱ ‹‹እንዲታተም ተፈቅዷል›› የሚል መልስ እንደተሰጣቸው የገለጸው ተመስገን፤” እናም ጋዜጣዋ አሁን እየታተመች ነው፡፡ ነገ ጠዋት ትወጣለች ብለንም እንጠብቃለን” በማለት ጽሁፉን አጠቃሏል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide