ሰመጉ የእስረኞቹ ጉዳይ ያሳስበኛል አለ

ሐምሌ ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የቀድሞ ኢሰመጉ የአሁኑ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ሰመጉ) በፖለቲካ መሪዎችና በጋዜጠኞች ላይ በቅርቡ ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ ያሳስበኛል አለ፡፡

ሰመጉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው የጸረ ሸብር ሕጉን በመተላለፍ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኃላ ጉዳያቸው በፍ/ቤት ሲታይ የቆየው በእነአንዱዓለም አራጌ ስም የተከፈተውም ሆነ ቀደም ሲል በተለያዩ ፋይሎች የተፈረደባቸው ኢትዮጽያዊያን ጉዳይ ከተለያዩ ምክንያቶች አንጻር እጅግ አድርጎ ያሳስበኛል ብሏል፡፡

ምንም እንኳን የጸረሸብር ህጉ አዋጅ ቁጥር 652/2009 ወትሮውንም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግስት ፣ኢትዮጽያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች የማይጣጣምና የዜጎችንም መብት እንደሚጥስ ቀደም ባሉት ጊዜያት አቋማችንን የገለጽን ቢሆንም የፍርድ ሒደቱን መንፈስ ላለመበረዝ ተጨማሪ መግለጫዎችን ከማውጣት ተቆጥበን ቆይተናል፡፡በተለይም ሐምሌ 6 ቀን 2004 ዓ.ም ጥፋተኛ በተባሉት ወገኖች ላይ ከፍተኛ ቅጣት ሲፈርድባቸው ታዝበናል ሲል ገልጾአል፡፡

የተጠርጣሪዎችን የማረሚያ ቤት ቆይታ ለመታዘብ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን ጠይቆ መከልከሉ፣የእድሜ ልክና ሌሎች ፍርደኞች ከተጠርጣሪዎች ጋር በአንድ ላይ እንዲታሰሩ መደረጉ፣የቅጣት ውሳኔ በተሰጠበት ቀን እያንዳንዱ በጥፋተኝነት የተፈረደበት ግለሰብ ስለቅጣቱ አስተያየት የመስጠት ሕጋዊና ሰብዓዊ መብቱ አለመከበሩ፣በአጠቃላይ ኀሳብን በነጻ የመግለጽ ነጻነት እየተሸረሸረ መምጣቱ እንደሚያሳስበው ጠቅሶአል፡፡

ሰመጉ በዚሁ መግለጫው የሰብዓዊ መብቶች የጀርባ አጥንት የሆኑት ኀሳብን በነጻነት መግለጽና ተደራጅቶ በፖለቲካ ትግል መሳተፍ በሕግም በአስተዳደራዊ ውሳኔ ሊታቀቡ እንደማይገባ ማስታወስ እንወዳለን ብሎአል፡፡

የዜጎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና የፍርሃት ድባብ ምንጭ የሆነው የጸረ ሸብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2009 እንደገና የሚታይበት ጊዜ አሁን መሆኑን ያሳሰበው ሰመጉ የአዋጁ አንዳንድ አንቀጾች ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግስት ፣ኢትዮጽያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ጋር እንደሚጣረሱ ታምኖ፣ከእውነተኛ አሸባሪ ይልቅ ንጹሃን ሰላማዊ ዜጎችና እንዲያሸማቅቅ ፣ዴሞክራሲያዊ መብቶችን እንዲገድብ ተደርጎ እየተተረጎመ ስለሆነ በፍጥነት ሊታረም ይገባል ብሎአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide