በቅርቡ በሲዳማ ዞን የተከሰተውን ችግር ተከትሎ የመንግስት ሰራተኞች ወደ እስር ቤት እየተጋዙ ነው

ሐምሌ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢሳት የደቡብ ዘጋቢ እንደገለጠው በሲዳማ ዞን በዳሌ ወረዳ ይርጋለም ከተማ 3 የልማት ሰራተኞች ከስራ የተባረሩ ሲሆን ፤ ከትናንት በስቲያ ከታሰሩት መካከል ደግሞ፣ የግብርና ሰራተኞች የሆኑት አቶ ዳዊት ኡጋሞና አቶ በለጠ በልጉዳ፣ የመዘጋጃ ሰራተኛ የሆኑት አቶ ዘሪሁን፣ መምህር ተስፋየ ተሻለ፣ መምህር አብዮት ዘሪሁን፣ መምህር በፍቃዱ ዱሞ፣ መምህር ለገሰ ገሰሰ፣ መምህር ዶልቃ ዱጉና እና ቀበሌ አመራሩ አቶ ካያሞ ፋቶ ይገኙበታል።

በአለታ ጭኮ ወረዳ ደግሞ የፌደራል ፖሊስ አባላት የወረዳውን ፖሊስ አዛዥ ክፉኛ በመደብደባቸው አዛዡ ሆስፒታል ተኝተዋል። አዛዡ የፖሊስ አባል መሆኑን መታወቂያውን በማውጣት ለፖሊሶች ቢያሳይም ፣ መታወቂያህን ለእናትህ አሳያት በማለት ቀጥቅጠው ደብድበውታል።  በሁሉም የሲዳማ ወረዳዎች ላይ የፌደራል ፖሊስ አባላት በብዛት ተብትነዋል። በዞኑ የሚገኙ ወረዳዎች የፌደራል ፖሊስ አባላትን ወጪ እንዲሸፍኑ በመጠየቃቸው ፣ ከክልሉ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል። የወረዳው ሀላፊዎች ለፖሊሶች ተብሎ የተያዘ በጀት በሌለበት ሁኔታ እንዴት ወጪያቸውን እንሸፍናለን የሚል ጥያቄ ቢያቀረቡም፣ የክልሉ መንግስት ለሴፍትኔት ተብሎ ከተያዘው ባጀት አውጥተው እንዲከፍሉ አዟል። አብዛኛው የሴፍትኔት ባጀት የሚያዘው ከአለም ባንክ በሚበጀት በጀት ነው።

በቀርቡ በአዋሳ እና በጪኮ ወረዳ የታሰሩት ወጣቶች ከአሸባሪው የግንቦት7 ጋር ተባብራችሁዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide