አቶ መለስ ቶሎ ስራ አይጀምሩም ተባለ

ሐምሌ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የመንግስት ኮምኒኬሸን ጽ/ቤት ሚኒስትር አቶ በረከት ስምኦን አቶ መለስ ሕክምናቸውን አጠናቀው በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምሩ፣ከሳቸው ጋር በተያያዘ በኢህአዴግ ውስት ሸኩቻ ተፈጥሯል የሚባለው ውሸት መሆኑን ዛሬ በጽ/ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትሩ ከጋዜጠኞች የቀረቡላቸውን ጥያቁዎች ማለትም አቶ መለስ በምን ሕመም እንደተያዙ፣የት ሆስፒታል እየታከሙ እንደሆነ፣በአሁኑ ሰዓት የት እንዳሉ “የቤተሰባቸውና የግላቸው ጉዳይ ነው” በሚል ምላሸ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

አቶ በረከትና እና ምክትላቸው አቶ ሽመልስ ከማል ትናንት ጋዜጣዊ መግለጫ የለንም በሚል ያባረሩዋቸውን ጋዜጠኞች  ዛሬ ከቀኑ 9፡30 ላይ ሰብስበው ፣ የአቶ መለስ ጤና በመታወኩ ውጭ ሀገር ሄደው በህክምና ላይ መሆናቸውንና ሰሞኑን ጤናቸው መሻሻል ማሳየቱን ገልጠው ሀኪማቸው እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው በገለጡት መሰረት አሁን በውጭ አገር እረፍት ላይ መሆናቸውን ጊዜው በውል ባይታወቅም በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚመለሱ ገልጠው ነገር ግን እረፍት እንዲያደርጉ ተመክረዋል ። እንደመጡ ስራ ላይጀምሩ ይችላሉ ብለዋል።

እናንተ ጋዜጠኞች ይህም ጉዳይ  የግል ጉዳይ መሆኑን የምታውቁ ይመስለኛል ያሉት አቶ በረከት፣ የህመማቸውን ሁኔታ፣ የሚታከሙበትን ሀገር እና ሆስፒታል ከደህንነት አንጻር አልገልጽም ብለዋል።

ከጋዜጠኞች ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ የሰጡት አቶ በረከት፣ እስካሁን ለመገናኛ ብዙሀን እና ለህዝብ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን መታመም ያልገለጥነው ፣ ኢህአዴግ ብዙ አትኩሮት ስላልሰጠው ነው ብለዋል።

በቅርቡ ስለአቶ መለስ ዜናዊ የጤንነት ሁኔታ ጥያቄ ቀርቦላቸው ይህ የኢሳትና የኢሳት ወሬ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ ከማል በመግለጫው ላይ ቢገኙም አንድም ቃል ሳይተነፍሱ ቀርተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህክምናቸውን በተሳካ ሁኔታ ጨርሰው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት የቀድሞው የአገሪቱ ርእሰ ብሄር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአቶ መለስን ህመም በተመለከተ ለኢሳት እንደተነጋሩት፣ በውጭ አገር እና በአገር ውስጥ የሚሰጡት አስተያየቶች መልካም ባለመሆናቸው፣ አቶ መለስ ተሽሎአቸው ወደ ስራ የሚመለሱ ከሆነ እነዚህን ሁሉ አስተያየቶች ተመልከተው የፖሊሲ ማስተካካያ ማድረግ እንደሚገባቸው፣ እርሳቸው ወደ ስልጣን ባይመለሱ እንኳ ኢህአዴግ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ እንዳለበት መክረዋል።

ላለፉት 20 አመታት የኢህአዴግ ደጋፊዎች  ለእርሳቸው ልዩ አክብሮት ይሰጡ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ነጋሶ ፣ የስልጣን ሽኩቻ ሊኖር እንደሚችልም ጠቁመዋል።

ዶ/ር ነጋሶ ከአለባቸው የእግር በሽታ ሙሉ በሙሉ ተሽሎአቸው ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ተናግረዋል።

 

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide