ለእስር ቤቶች ግንባታ የሚመደበው በጀት በየዓመቱ ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ ነው

ሰኔ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ መንግስት ለእስር ቤቶች ግንባታ በየዓመቱ የሚመድበው ባጀት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ጠቆሙ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከ2003 እስከ 2005 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት መንግስት  ለፌዴራል እስር ቤቶች ግንባታ ብቻ በድምሩ 415 ሚሊየን 153 ሺ100 ብር መድቧል፡፡

በ2003 በጀት ዓመት 13 ሚሊየን ለግንባታ( ካፒታል ወጪ) የመደበ ሲሆን ይህ ቁጥር በ2004 ዓ.ም ወደ 193 ሚሊየን ብር አሻቅቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት ገና በረቂቅ ደረጃ ለፓርላማ በቀረበው የ2005 በጀት ላይ ለፌዴራል እስር ቤቶች ለማሰፋፊያና ግንባታ ብቻ የተያዘው በጀት 210 ሚሊየን ብር ደርሷል፡፡

በግንባታ ላይ የሚገኙት የፌዴራል እስር ቤቶች መካከል የድሬዳዋ ሁሉአቀፍ እስር ቤት የታራሚዎች መኖሪያ ቤት ሕንጻ፣የአዲስአበባ እስር ቤት  ጠቅላላ ሆስፒታልና የታሳሪዎች  መኖሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታ፣በሸዋሮቢት  እስር ቤት  የታሳሪዎች  መኖሪያ ቤት ሕንጻ  ግንባታ ፣የዝዋይ እስር ቤት የታራሚዎች መኖሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታ ይጠቀሳሉ፡፡

በፖለቲካ ሰበብ የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣት እስር ቤቶች እንዲስፋፉ አድርጓል። አንድ የእስር ቤት አስተዳደር ባለስልጣን ለኢሳት ዘጋቢ እንደገለጡት፣ የአንድ አገር ስርአት ሲበላሽ ወይም አምባገነንነት ሲበዛ መንግስት በቅድሚያ የሚታየው እስር ቤቶችን ማስፋፋት ነው፤ ሰዎች ሁሉ በእስር ቤት ከታጎሩ የተቃውሞ ድምጽ አያሰሙም ብሎ ያስባል ብለዋል። መንግስት ከምርጫ 97 በሁዋላ ካስፋፋቸው መስሪያ ቤቶች መካከል እስር ቤቶች በቀዳሚነት እንደሚጠቀሱ ባለስልጣኑ ተናግረዋል።

ኢሳት በትናንት ዘገባው የቃሊቲ እስር ቤት በመሙላቱ የፖለቲካ እስረኞች ወደ ቁሊቶ እስር ቤት እንዲዛወሩ መደረጉን ገልጦ ነበር። በመጪው ክረምት በርካታ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና ጋዜጠኞችም እንደሚታሰሩ ኢሳት መረጃዎች እንደደረሱት መግለጡ ይታወሳል።

የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት በቅርቡ ባወጣው የ2011 የሰብዓዊ መብት ሪፖርት በኢትዮጵያ የሚገኝ አንድ እስረኛ የቀን በጀቱ 8 ብር ወይም 0.46 ዶላር መሆኑን በመጥቀስ ይህ ገንዘብ እስረኛውን  የቀን የምግብ፣የንጽህናና የጤና ወጪውን ለመሸፈን የማያሰችል ነው ብሏል፡፡በዚሁ ጉዳይ ከፌዴራል እስር ቤቶች የተገኘው መረጃ ችግሩ መኖሩን አረጋግጦ የእስረኞችን ቀለብ ለማሻሻል በእስር ቤቱ በኩል ለመንግስት የቀረበው የማሻሻያ ጥናት ባለመፈቀዱ በቀለብ አቅርቦት ላይ ቀላል የማይባል ችግር እየገጠመው መሆኑን ይገልጻል፡፡

ባለፈው ወር አጋማሸ ላይ ይፋ የሆነው የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት በኢትዮጵያ ክልሎችን ጨምሮ በጠቅላላው 120 እስር ቤቶች መኖራቸውን፣በውስጣቸውም 86 ሺ ያህል ታራሚዎች መኖራቸውን፣ ከነዚህ ውስጥ 2ሺ 474 ያህሉ ሴቶች መሆናቸውን፣546 ሕጻናት ያለጥፋታቸው ከእናቶቻቸው ጋር ታሰረው እንደሚገኙ ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide