የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጋዜጠኛና መምህርት ርእዮት አለሙን አቤቱታ አደመጠ

ሰኔ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዛሬ ረፋዱ ላይ የመሀል ዳኛው አቶ ዳኘ መላኩ፣ የቀኝ ዳኛው በላቸው አንሺሾና ስማቸው ያልተገለጠው ግራ ዳኛው በመሩት ችሎት ላይ የርእዮት ጠበቃ የሆኑት አቶ ሞላ ዘገየ እና አቃቢ ህጉ አቶ ብርሀኑ ወንድማገኝ ተከራክረዋል። የርእዮት አባት የሆኑት አቶ አለሙ ገበቦ በረዳት ጠበቃነት ተሳትፈዋል።

ጠበቃ ሞላ ዘገየ ደንበኛቸው ርእዮት አለሙ በህገመንግስቱ አንቀጽ 29 በተሰጣት መብት መሰረት የጋዜጠኝነት ሙያዋን ስራ በይፋ ያከናወነች እንጅ ምንም አይነት ጥፋት አለመስራቱዋን ገልጠው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተከላከይ እንኳን ሊያስብላት የማያስችል መረጃ አቃቢ ህግ አቅርቦ ባስደመጠበት ሁኔታ ይባስ ብሎ የጥፋተኝነት ውሳኔ ወስኖባታል ስለዚህ ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ፍትህ እንዲሰጠኝ እጠይቃለሁ ብለዋል።

ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሙያ ምስክሮችን ዶ/ር መረራ ጉዲናንና ዶ/ር ያቆብ ሀይለማርያምን እንዳይደመጡ አድርጎ ከልክሎ የመከላከል መብቷን አሳጥቷታል ብለዋል።
አቃቢ ህግ ብርሀኑ ወንድማገኝ የክስ ቻርጁን እንደገና በንግግር አቅርበዋል። ዳኛ ዳኘ መላኩ ለሁለቱም አካላት የማጣሪያ ጥያቄ አቅርበዋል። ርእዮት አለሙ የመናገር እድል ጠይቃ ፣ ከኤልያስ ክፍሌ ጋር በጋዜጠኝነት ስራዋ መገናኘቱዋን፣ በሪፖርተርነት ለ 2 ወራት መስራቱዋን እና በመጀመሪያው ወር 1500 ብር ተዋውላ በባንክ እንደተላከላት እንዲሁም በሁለተኛው ወር ደግሞ 2521 ብር እንደተከፈላት ስትናገር ዳኛው ግራ ገብቷቸው “ብሩ በዶላር ነው በብር?” ሲሉ ጠይቀዋል። ርእዮትም “በኢትዮጵያ ብር” ብላ ስትመልስላቸው ተደንቀው ወደ አቃቢ ህግ በመዞር ” ከግንቦት7 እና ከኤርትራ መንግስት ብር ተቀብላለች ያልከው ይህን ነው ወይስ ሌላ የያዛችሁት ማስረጃ አለ?” ብለው  ጠይቀዋል። አቃቢ ህጉም  ” ኤልያስ ክፍሌ በፓርላማ አሸባሪ ባይባልም ከአሜሪካ ወደ ኤርትራ እየሄደ እርሱ ነው የሚያደራጃቸው ፣ ጋዜጠኝነቱ ሽፋን ነው” በማለት መልሶአል ፡ ርእዮትም ” ክቡር ፍርድ ቤት እንኳን በእኔ ይቅርና በኤልያስ ላይም ምንም ሽብርተኛ የሚያስብል ማስረጃ አልቀረበም ። መዝገቡ ላይ ታዩታላችሁ ፣ ለሚዲያ ያወራውን ሰላማዊ ሀሳብ ነው በማስረጃነት ያቀረቡት” በማለት መልሳለች። አቃቢ ህግ ብርሀኑም ርእዮት የእነ ኤልያስን አላማ  ደግፋለች በማለት ለችሎቱ ተናግሯል።

በችሎቱ ላይ የርእዮት ቤተሰቦች በርካታ ጋዜጠኞች እና የዲፐሎማቲክ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

የሁለቱን ወገን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤት ለማክሰኞ ለውሳኔ ሀምሌ 10 ቀን 2004 ዓም የጊዜ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን፣ ከጊዜ ቀጠሮ በፊት የክርክሩ ቃል ወደ ጽሁፍ ተገልብጦ እና አጠቃላይ መዝገቡ ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ታዞ እንዲመጣለት አዙዋል። በጊዜው ካልደረሰን ግን ቀኑን ወደፊት እናሸጋሽገዋለን ብሎአል።

የአረቡ አብዮት በተነሳ ማግስት የመለስ መንግስት ርእዮት አለሙን እና ጋዜጠኛ ውብሸት ታየን ጨምሮ  ፖለቲከኛ ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄርንና ሂሩት ክፍሌን ለአለፈው አንድ አመት በእስር ቤት ማጎሩ ይታወሳል። ተከሳሾች ጠንካራ ማስረጃዎች ሳይቀርቡባቸው ከ14 አመት እስከ 19 አመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መወሰኑ ይታወሳል። ጋዜጠኛ ውብሸት ታየ፣ ፖለቲከና ዘሪሁን ገብረእግዚአብሄርና ሂሩት ክፍሌ የይቅርታ ፎርም ሞልተው ማስገባታቸው መዘገቡ ይታወሳል። ጋዜጠኛና መምህርት ርእዮት ይቀርታ ለመጠየቅ ፈቃደና ባለመሆኑዋ ነው ይገባኝ ጠይቃ በመከራከር ላይ ያለቸው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide