የፖለቲካ ግብ ያለውን ማስታወቂያ የሚከለክለው ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

ሰኔ ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፖለቲካ ፓርቲዎች ( ድርጅቶች ) የፖለቲካ ግብ ያለው ማስታወቂያ እንዳያሰራጩ የሚከለክለው ረቂቅ አዋጅ በብሮድካስት ባለሥልጣን አርቃቂነት በሚኒስትሮች ም/ቤት ጸድቆ ትናንት ለፓርላማ ቀረበ፡፡

ረቂቅ አዋጁ የፖለቲካ ድርጅቶች የሚያደርጉትን የአድራሻ ለውጥ፣የስብሰባ ጥሪ እና መሰል ማስታወቂያ እንደተጠበቀ ሆኖ የፖለቲካ ግብ ያለው ማስታወቂያን በመገናኛ ብዙሃን እንዳይተላለፍ ይከለክላል፡፡ አዲሱ ህግ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት የመገናኛ ብዙሃንን ማስታወቂያዎች ስፖንሰር ማድረግ እንደማይችሉ  ደንግጓል፡፡

ህጉ ተቃዋሚዎችን ሆን ተብሎ ለመምታት ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑን አንድ የተቃዋሚ አባል ተናግረዋል። ገዢው ፓርቲ ማስታወቂያዎችን የሚያስነግረበት የመገናኛ ብዘሀን በርካታ ሆነው ሳለ ተቃዋሚዎች አልፎ አልፎ እንኳ በጋዜጦች አንዳንድ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ማስታወቂያ እንዳያወጡ መከልከሉ ገዢው ፓርቲ የገባበበትን የፍርሀት ደረጃ ያሳያል ብለዋል። ትንሹም ትልቁም ነገር እያስደነበረው ነው የሚሉት ፖለቲከኛው “መንግስት ለምን የፖለቲካ ድርጅቶችን በአዋጅ እንደማያፈርስ አይገባኝም፣ ምናልባት እርዳታው እንዳይቋረጥበት ፈልጎ ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት የፕሬስ አሳታሚዎችን ክፉኛ አስደንግጦ የነበረው የማስታወቂያ ረቂቅ አዋጅ ዛሬ ለፓርላማው ተሻሸሎ ቀርቧል፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የፕሬስ ሚዲያዎች በየእለቱ ከሚያወጡት ጋዜጣ ወይም መጽሔት የማስታወቂያ ሸፋን ከ30 በመቶ መብለጥ የለበትም የሚል ረቂቅ አዋጅ ከመቅረቡ ጋር ተያይዞ በተለይ በአሁኑ ሰዓት ከማስታወቂያ ገቢ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ሪፖርተር፣ፎርቹን፣  ካፒታል፣አዲስአድማስ የመሳሰሉ ጋዜጦች ከፍተኛ ተቃውሞ ካሰሙ በሁዋላ ባልተለመደ መልኩ አዋጁ በረቂቅ ደረጃ እያለ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡  ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከዚህ በፊት ከቀረበው በተቃራኒ በአንድ ጋዜጣ/መጽሔት  በአንድ ዕትም  እስከ 70 በመቶ ማስታወቂያን ፈቅዷል፡፡ መንግስት በማስታወቂያ የሚተዳደሩት ጋዜጦች በህይወት በመቆየታቸው ከሚጎዳ ይልቅ ይበልጥ ይጠቀማል የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉ። ጋዜጦቹ በመንግስት ላይ ጠንካራ ትችት የሚያቀርቡ ባለመሆናቸው መንግስት የፕሬስ ነጻነትን እንደሚያከብር ለማሳያነት ሲጠቀምባቸው ቆይቷል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide