ለልማት የሄዱ ዲያስፖራዎች ፦”የመንግስት ያለህ!”እያሉ ነው

ግንቦት ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “የመንግስትን የልማት ጥሪ አምነን ወደ አገራችን  ከገባን በሁዋላ  በሙስና እየተንገላታንና እየተሰቃየን ነው” ሲሉ  ለሪል ስቴት ግንባታ   ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑ  ዲያስፖራዎች  እሮሮ እያሰሙ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ  ዲያስፖራው ወደ አገሩ ገብቶ በኢንቨስትመንት አስንዲሳተፍ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ ሰምተን ነው ለዓመታት በምቾት ስንኖርባት አሜሪካ ለልማት ወደ አገራችን ያቀናነው ይላሉ-የ ጂ. ኤም.ኤ.ኤስ ሪል ስቴት አክስዮን ማህበር አባላት።

ከዚያም በአምስት ኪሎ ከድህረ-ምረቃ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት  የሚገኙትንና ንግድ ሥራ ሲያካሂዱባቸው የቆዩትን የቀበሌ ቤቶች በሪል ስቴት ለማልማት መደራጀታቸውን የሚናገሩት እነዚሁ የቀድሞ የዲያስፖራ አባላት፤ ለዚህም አስፈላጊ የሆኑትን መስፈርቶች በማሟላት ፕሮፖዛላቸውን  ለአዲስ አበባ ሊዝ ቦታዎች አፈፃፀም ጽህፈት ቤት ማስገባታቸውን ጠቁመዋል።

ጽህፈት ቤቱም ፦”ቦታው ለግንባታ የሚውል ከሆነ መስፈርቱን ስላሟላችሁ ቅድሚያ የሚሰጣችሁ እናንተ ናችሁ፤ ጥቂት ታገሱ” እያለ ሲያጉላላቸው መቆየቱን የጠቀሱት የአክስዮን አባላቱ፤”እኛ በህጋዊ መስመር ውሳኔውን እየጠበቅን ሳለ፤ ህግን በጣሰ አሠራር ለራዲካል አካዳሚ ባለቤት ለአቶ ገብረ ሥላሴ በየነ ተሰጥቷል ተባልን ብለዋል።

 

አቶ ገብረሥላሴ ያመለከቱት ከነሱ በሁዋላ እጅግ ዘግይተው እንደሆነ እና  ቦታውን ሊያገኙ የሚችሉበት ምንም ዓይነት የህግ  አግባብ እንደሌለ  ያስረዱት የአክስዮን ማህበሩ አባላት፤ “ቦታው ለነሱ አይገባም ከተባለ ግልጽ ጨረታ ሊወጣበት እንጂ በአቋራጭና በሙስና  ለማይገባው ሰው ሊሰጥ እንደማይገባ ተናግረዋል።

-“አቶ ገብረ ሥላሴ  የተሰጣቸውንስ ትምህርት ቤት  መቼ በሥርዓት ተጠቀሙበት?”ሲሉም አክለዋል።

እንደ አክስዮን ማህበሩ አባላት ገለፃ አቶ ገብረሥላሴ  ከህግ አግባብ ውጪ ከፍ ያለ ጥቅም እያገኙ ያሉ ግለሰብ ናቸው።በባለቤትነት በሚመሩት በራዲካል አካዳሚ ግቢ ውስጥ የነበሩ ሁለት የቀበሌ ቤቶችን በህገ ወጥ መንገድ አፍርሰው ለራሳቸው እየተገለገሉባቸው ቢሆንም፤እስካሁን የጠየቃቸው አንድም ባለስልጣን የለም።

የአቶ ገብረስላሴ ራዲካክ አካዳሚ ከጀማሪ እስከ 12 ኛ ክፍል 300 ታዳጊ ወጣት ተማሪዎችን ያቀፈ ቢሆንም፤ ከዚያው በተጓዳኝ በህገ ወጥ መንገድ  ቢራ እንደሚያከፋፍል ተጠቁሟል።

“ታዳጊ ወጣቶች በሚማሩበት ትምህርት ቤት ውስጥ ቢራ ማከፋፈል ህጉ ይፈቅዳልን?” ሲሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ በአግራሞት ጠይቀዋል።

ከዚህብ ባሻገር በ አካዳሚው ውስጥ ያሉ ተማሪዎች ከ300 የማይበልጡ ቢሆንም፤  ለሊዝ ቦርዱ የቀረበው መረጃ ከ 2000 እስከ 3000 የሚገመቱ ተማሪዎች እንደሚማሩ ተደርጎ ነው።

“ይህ አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ እኛ በህጋዊነት የጠየቅነው ቦታ በአቋራጭ ለእርሳቸው መሰጠቱ እጅግ አሳዛኝ ነው ያሉት እኚሁ የቀድሞ ዲያስፖራዎች፤ በህገ-ወጥ አሰራር እና በሙስና ትስስር መብታችን ተነጥቋል ሲሉ ምሬት እያሰሙ ይገኛሉ።

ከዚህ ሁሉ በሁዋላ ግንቦት 13 ቀን 2004 ዓ.ም ከወረዳ 6 ሥራ አስኪያጅ ጽ/ቤት በሚል የራስጌ አድራሻ ባለበት ወረቀት ላይ የተፃፈና- ቁጥር የሌለው፤ የግርጌ ማህተሙ ትክክለኛነትም አጠራጣሪ የሆነ  ደብዳቤ ከሦስት ቀን በፊት ከአንድ ግለሰብ  እንደተመለከቱ የሪል ስቴት አባላቱ ተናግረዋል።

“ደብዳቤው ለኛ ለባለ አድራሻዎቹ ለምን በቀጥታ እንዳልተፃፈልን አልገባንም ያሉት” እኚሁ የቀድሞ ዲያስፖራ አባላት፤ የደብዳቤው ይዘት በአስር ቀናት ውስጥ ቦታውን እንድትለቁ” የሚል ማስጠንቀቂያ እንደሆነ አመልክተዋል።

 

በሁኔታው እጅግ ያዘኑት የሪል ስቴት አባላቱ፦“በዚች አገር በህገወጥ አሰራርና በሙስና የሚፈፀመውን ተግባር ተመልክቶ የሚመለከተው አካል እርምጃ እንዲወስድልን አቤቱታችንን አሰሙልን” ሲሉ ለፍኖተ ነፃነት ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል።

የሪል ስቴት አክሲዮን ማህበር አባላቱ አክለውም፦“በአሜሪካን አገር የምንኖር ነበርን፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ ዲያስፖራው ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲያለማ ጥሪ ሲያቀርቡ ሰማን፡፡ እኛም የጠ/ሚኒስትሩን ቃል አምነን  አገራችንን ለማልማትና ራሳችንን ለመጥቀም በሚል ገንዘባችንን ከሰከስን ። በመጨረሻም እንዲሁ ቀረን”ብለዋል።

“ከውጪ ከመምጣታችን በፊት፦ እንዴት ኢህአዴግን አምናችሁ ትሄዳላችሁ? ምኑን አምናችሁ ገንዘባችሁን ታፈሳላችሁ? በሚል  ከዲያስፖራው ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞን ነበር” ያሉት እነኚሁ የቀድሞ የዲያስፖራ አባላት፤ እኛ ግን ሄደን ማረጋገጥ አለብን ብለን መጣን። መጥተን የገጠመን ግን እጅግ አሳዛኝ ነው”ብለዋል።

አያይዘውም፦” የበታች ኃላፊዎች በሙስናና በህገወጥ አሠራር የተሳሰሩና የተመሳጠሩ ናቸው፡፡ አንዱ የሠራውን ጥፋት ሌላው ሊያርመው አይፈልግም፡፡ በየሄድንበት የመስተዳድር መዋቅር የሚደርስብን ማመናጨቅና ግልምጫ ያሳዝናል። አቤቱታችንንም መስማት አይፈልጉም፡፡ በህገወጥ መንገድ በተቀነባበረ የሐሰት ሰነድ መብታችን  ለሌላ አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡ የጠየቅነውን ቦታ በህጋዊ መንገድ ለመውሰድ  ስንሞክር ፤በባለሥልጣን ለማስፈራራት ይሞከራል” በማለት  የሙስናውን መክፋትና ውስብስብ መሆን በዝርዝር አስረድተዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የ አቶ ገብረሥላሴ በየነን አስተያዬት ለማካተት የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

“በአገር ቤት በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የተመቻቸ ሁኔታ አለ” የሚለውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሮፓጋንዳ በመስማት በተለያዩ ጊዜያት ጥሪታቸውን አሟጠው ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑ የዲያስፖራ አባላት፤ በውስብስብ ቢሮክራሲና በሙስና ባዶ እጃቸውን ቀርተው ለጸጸት እየተዳረጉ እንደሚገኙ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide