የኢትዮጵያ መንግስት የአረብሳት ባለስልጣናትን ተማፀነ

ግንቦት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች ድምጾች በቴሌቪዥን የማያቀርብ ከሆነ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚተላለፈውን ስርጭት የኢትዮጵያ መንግስት ለማቋረጥ ዝግጁ መሆኑን መግለጡ ታወቀ::

የኢሳት የመረጃ ምንጮች እንደገለጡት የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄውን ያቀረበው ለአረብሳት ነው።   መንግስት በመጀመሪያ በአረብ ሳት ሲተላለፍ የነበረውን  ኢሳትን ፣ ቀጥሎም የኤርትራን ቴሌቪዥን ለማፈን ሙከራ ማድረጉን ተከትሎ፣ ከአረብ ሳት ባለስልጣናት ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር። የአረብ ሳት ባለስልጣናትም የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ ሲያስጠነቅቁት ቆይተዋል። ይሁን እንጅ መንግስት ከዚህ ድርጊቱ ሊቆጠብ ባለመቻሉ የአረብሳት ባለስልጣናት የኢትዮጵያን እና የኤርትራን የአረብሳት ስርጭቶች እንዲቋረጡ አድርገዋል።

ውዝግቡን በንግግር ለመፍታት ጥረት ያደረጉት የአረብሳት ባለስልጣናት ከኢትዮጵያ መንግስት ያገኙት መልስ አሳዝኖአቸው እንደነበር ታውቋል። የኢትዮጵያ መንግስት ኢሳትን የመሳሰሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች ዝግጅቶች በአረብ ሳት በሚተላላፈው የኤርትራ ቴሌቪዥን ላይ የማይቀርቡ ከሆነ ፣ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚተላለፈውን ስርጭት ለማቋረጥ ዝግጁ ነኝ የሚል ቅድመ ሁኔታ ለኩባንያው ቢያቀርብም የኤርትራ መንግስት ግን የኢትዮጵያን ቅድመ ሁኔታ አልተቀበለውም። የኤርትራ መንግስት  ” የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ኤርትራ የሚልከውን ስርጭት ከፈለገ ከአንድ ሰአት ወደ 24 ሰአት ማሳደግ እንደሚችል እና በስርጭቱ ምንም እንደማይከፋ፣ በጣቢያው ላይ የሚተላላፉ ዝግጅቶችን የሚወስነው ግን ራሱ መሆኑን በመግለጥ የኢትዮጵያን መንግስት መደራደሪያ ውድቅ አድርጓል።

በኢትዮጵያ መንግስት አቋም የተበሳጩት የአረብ ሳት ባለስልጣናት ለ4 ወራት ያክል በራቸውን በመዝጋት የኢትዮጵያን መንግስት ባለስልጣናት ለመቀበል አሻፈረን ብለው ነበር። የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ከአራት ወራት ልመና በሁዋላ  ለአረብ ሳት ባለስልጣናት ከአሁን በሁዋላ አፈና እንዳማያካሂዱ የጽሁፍ ማረጋጋጫ በመስጠታቸው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን  ወደ አየር እንዲመለስ ተፈቅዶለታል።

አንድ የአረብ ሳት ባለስልጣን ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ከተገናኙ በሁዋላ በባለስልጣኖቹ ድርጊት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሁኔታ ማዘናቸውን መናገራቸውን ምንጮች አስታውቀዋል።

የኤርትራ ቴሌቪዥን የኢሳትን ስርጭት ከኢንተርኔት ላይ በመውሰድ አልፎ አልፎ እንደሚያሰራጭ ይታወቃል።

አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት ፕሬሱን ለማፈን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ አውግዘዋል። የመለስ መንግስት ግን ሳተላይት ስርጭቶችን ከማፈን አልፎ በአገር ውስጥ የሚታተሙ አነስተኛ ስርጭት ያላቸውን ጋዜጦች ሳይቀር ለመቆጣጠር አዲስ የማተሚያ የንግድ ውል ማውጣቱ ይታወቃል። በኢንተርኔር የሚሰራጩትን መረጃዎች ለማፈንም አዲስ የቴሌ ህግ በማርቀቅ ላይ ይገኛል። 99 ነጥብ 6 በመቶ የሆነ የህዝብ አመኔታ አግኝቼ ተመርጫለሁ የሚለው የመለስ መንግስት  ፣ ነጻ ሀሳብን ከሚያፍኑ የአለም አገሮች መካከል በግንባር ቀደምነት ይጠቀሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide