ጋዜጠኛ ርእዮት አለሙ ይግባኝ ጠየቀች

ግንቦት ፴ (ሰላሳ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአቶ መለስ ዜናዊ መንግሥት አሸባሪ ተብላ 14 ዓመት ጽኑ እስራት የተፈረደባትና  33 ሺህ ብር የተቀጣችው ጋዜጠኛና መምህርት ርዮት ዓለሙ ከመንግሥት በኩል በተዘዋዋሪ የቀረበላትን የይቅርታ ጥያቄ ችላ ትናንት ለጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቀረበች፡፡

ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበችው አቤቱታ ላይ ጋዜጠኛ ርዮት ምንም ዓይነት ወንጀል እንዳልሰራች ገልጣለች። ይልቁኑም መንግሥት በእርሷ ላይ ወንጀል መፈጸሙን፣ ፈጸመች የተባለችው ወንጀል እና ቀረበባት ማስረጃ የሀሰት ምስክርና የቀን ተቀን ተራ የጋዜጠኝነት ሥራ የስልክ ንግግር መሆኑን እና ምንም ዓይነት ተጨባጭ ማስረጃ ሳይቀርብባት ተከላከይ መባሏ አግባብ አለመሆኑን በጽሑፍ ገልጣለች።  “ይህም ቢሆን በበቂ ሁኔታ ክሱን አስተባብዬ በማስረጃ ብከራከርም /ብከላከልም/ ከከፍተኛው ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ፍትህን ላገኝ አልቻልኩም” ብላለች፡፡

የይግባኝ አቤቱታውን የተመለከተው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳዩ ይግባኝ የሚያስጠይቅ መሆኑን ወስኖ አቤቱታውን በጥልቀት ለመመርመር ለሰኔ 15 ቀን 2004 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቶ ችሎቱ ተበትኗል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide