ሥራ ተቋራጮች ለህዳሴው ግድብ ቃል ከገቡት ውስጥ የሰጡት 10 በመቶውን ብቻ በመሆኑ መንግስት አቸኳይ ስብሰባ ጠራቸው

ግንቦት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በስብሰባው የተገኙት ተቋራጮች ፦”መንግስት ፕሮጀክቶችን ሁሉ ለቻይና እና ለጃፓን ተቋራጮች እየሰጠ ባለበት ሁኔታ መሥራት አልቻልንም” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በተለያዩ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ሥራ ተቋራጮች ለህዳሴው ግድብ ቃል ከገቡት 150 ሚሊዮን ብር ውስጥ እስካሁን የለገሱት 10 በመቶውን ማለትም 15 ሚሊዮን ብር ብቻ እንደሆነ   ተዘግቧል፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩና  በማኅበር የተደራጁ 1 ሺ 400 ተቋራጮች ሰሞኑን በተጠራ አንድ ስብሰባ ላይ፤ ሥራ እየሠሩ አለመሆናቸውን እንዲሁም የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም ምንም ድጋፍ ስለማያደርግላቸው በችግር ውስጥ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

ግንቦት 25 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በተደረገው በዚሁ  ስብሰባ  ላይ ፦እነሱ አገርን የሚመለከት ማንኛውንም ዓይነት ነገር ሲመጣ ግንባር ቀደም ሆነው ቢቀርቡም፣ መንግሥት ግን አንድ የኮንስትራክሽን ሥራ ለማሠራት ሲፈልግ፣ ፕሮጀክቱን የሚሰጠው ለቻይናና ለጃፓን ተቋራጮች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በአንድ ሥራ ላይ ብቻ  እየተወሰኑ ለበርካታ ወራት ሥራ ለመፍታት መገደዳቸውን የጠቆሙት ተቋራጮቹ፣ ሚኒስቴሩ ችግራቸውን እንዲመለከትላቸውና ፕሮጀክቶችን የሚያገኙበትን መንገድ እንዲያመቻችላቸው ተማጽነዋል።

ይህ ቢደረግላቸው  እየገቡበት ካሉበት ኪሳራ ሊወጡ የሚችሉበት መንገድ ሊፈጠር እንደሚችል አስረድተዋል፡፡

እንደ ሪፖርተር ዘገባ ተቋራጮቹ እንዲሰበሰቡ የተፈለገበት ዋናው ጉዳይ፤ ለህዳሴው ግድብ ቦንድ ለመግዛትና በስጦታ ለመስጠት ቃል የገቡት 150 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ እስከ ቅርብ ቀን ድረስ ገቢ ያደረጉት ከአሥር በመቶ ባለመብለጡ ሳቢያ ነው፡፡

ስብሰባውን በመምራት ተቋራጮቹን ያወያዩት  ከከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የተወከሉ ሁለት አቶ አማረ አስገዶም እና  የድጋፍ ሰጭ ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ብሩ ናቸው።

አወያዮቹም፦ ተቋራጮቹን፦ ‹‹ምን እናድርግ?›› በማለት በገቡት ቃል መሠረት ክፍያውን ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ተግባራዊ የሚያደርጉበትን መንገድ ከራሳቸው ለማፈላለግ ጥያቄ አንስተዋል፡፡

ከተሰብሳቢዎቹ  መካከል፦ ‹‹ምንም ይሁን ምንም ቃል የገባነውን እንፈጽማለን›› ያሉት ተቋራጮች  ፤ ሚኒስቴሩ ቤቱ ግን ችግራቸውን ሊገነዘብላቸውና  ሊያበረታታቸው  እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

መዋጮውንም በሚመለከት ‹‹ባለን የተቋራጭነት ደረጃ፣ ለማዋጣት በወጣልን መስፈርትና የሥራ መጠን መሠረት ብንከፍል የተሻለ ነው፤›› በማለት የአከፋፈሉ ሁኔታ ዳግም በደንብ ሊጤን ይገባዋል ያሉ ተቋራጮችም ተሰምተዋል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች በመጨረሻም ተቋራጮቹ  አከፋፈላቸው የተዳከመ መሆኑን ጠቁመው፣ የገቡትን ቃል በወቅቱ እንዲያጠናቅቁ  ማስጠንቀቂያ አዘል ምክር አስተላልፈዋል።

ሀላፊዎቹ ፦”ቃል የገባችሁትን  በወቅቱ ማጠናቀቅ አለባችሁ!” በማለት ለተቋራጮቹ ማሣሰቢያ ከመስጠት ውጪ  ተቋራጮቹ  በመንግስት በኩል እንዲስተካከሉላቸው ላነሷቸው ጥያቄዎችና ቅሬታዎች ምንም ያሉት ነገር የለም።

በሌላ ዜና ደግሞ አቶ መለስ የአባይን ግድብ አስጀምረው ሳያስጨርሱ ስልጣን እንዳይለቁ የሚጠይቁ ማስታወቂያዎች በመለጠፍ ላይ ናቸው። የኢሳት የመረጃ መንጮች እንደገለጡት አቶ መለስ ከ3 አመት በሁዋላ በኢህአዴግ የመተካካት ፖሊሲ መሰረት ስልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ መናገራቸው ይታወቃል። ይሁን እንጅ ኢህአዴግ ገና ከአሁኑ አቶ መለስ የአባይን ግድብ ጅማሮ ሳያጠናቅቁ ስልጣን እንዳይለቁ የሚጠይቁ ባነሮችን እያሰራ በመኪናዎች ላይ ሳይቀር ማስለጠፍ ጀምሯል። ኢህአዴግ ጥያቄው ከህዝብ የመታ ለማስመሰል እየሞከረ ነው ያለው ዘጋቢያችን፣ በቅርቡም በአዲስ አበባ ” መሪያችን የጀመሩትን ሳይጨርሱ እንዳይሄዱ እንጠይቅዎታለን።” የሚል ታፔላ በአዲስ አበባ ለመስቀል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብሎአል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide