ግንቦት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያውን ከደቡብ አፍሪካው “ባፋና ባፋና” ጋር ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1 ለ 1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያዬ:: የሴት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ከ 1000 ብር እስከ 2000 ብር ተሸለሙ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ በመጫዎት ያገኘው ውጤት ብዙሀኑን የስፖርት ቤተሰብ አስደስቷል።
በመጀመሪያው 45 ደቂቃ ክፍለ-ጊዜ ‘ባፋና ባፋናዎች’ አልፎ አልፎ ያደረጓቸው አስደንጋጭ ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ብርቱ ጥረት ጎል ሳይሆኑ ከሽፈዋል።
በ 27 ኛው ደቂቃ ላይ የደቡብ አፍሪካ ተከላካዮች በግራ የተከላካይ መስመር አካባቢ አንድ ሁለት ለመቀባበል ሲሞክሩ በመሀከል በመግባት ኳሷን የነጠቀው ቆፍጣናው ሳላሀዲን ፤ኳሷን በፍጥነት ወደፊት በመግፋትና ከፊት ለፊቱ ደርሶ ኳስ ሊያስጥለው ይታገል የነበረውን ተከላካይ በማታለል በቀኝ እግሩ አክርሮ የመታት ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ ከመረቡ ጋር ተዋህዳለች።
የመጀመሪያውን 45 ደቂቃ ክፍለ ጊዜ በዚሁ የሳልሀዲን ጎል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 1 ለባዶ መምራት ችሏል።
ከዕረፍት በሁዋላ ሙሉ በሙሉ በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታን የመረጡት ደቡብ አፍሪካዎች በ 64 ኛው ደቂቃ ላይ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውስጥ የኢቨርተን ሞተር የሆነው ፒናር ከቀኝ መስመር ያሻማትን ኳስ ከደቡብ አፍሪካ አጥቂዎች አንድኛው በጭንቅላት በመግጨት ከመረቡ ጋር አገናኛት ሲባል፤ የብሔራዊ ቡድናችን ጎል ጠባቂ በእግሩ አውጥቷታል።
ይሁንና ባለ በሌ ሀይላቸው ጫና ፈጥረው ሲጫዎቱ የነበሩት ባፋና ባፋናዎች ከዚች ሙከራ በሁዋላ ብዙም ሳይቆዩ አቻ ያደረገቻቸውን ጎል አግኝተዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ከመጫዎቱ አኳያ የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የስፖርት ቤተሰቦች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት፦”እኛ ከደቡብ አፍሪካዎች በተሻለ መልኩ ዝግጅት አድርገናል”በማለት ቃለ-ምልልስ ሰጥተው ነበር።
በተለይ የሳልሀዲን ጎል በበርካታ ስፖርት አፍቃሪዎች ዘንድ አድናቆትን አግኝታለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የግብጽ አቻቸውን 4 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት፣ታንዛንያን ደግሞ 2 ለ 1 በማሸነፍ አስደናቂ ውጤት እያስመዘገቡ ለመጡት የ ኢትዮጵያ የሴት ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች በቅፅል ስማቸው- ለሉሲዎች ፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንድ ላይ በመሆን ለእያንዳንዳቸው ከ 1000 ሺህ ብር እስከ 2000 ሺህ ብር የሚያወጣ ቦንድ ገዝተውላቸዋል።
1000 ብር ፤ በወቅቱ ምንዛሬ መሰረት ፤ከ 40 ፓውንድ፣ ከ 50ዩሮ ወይም ከ 67 የ አሜሪካን ዶላር ጋር እኩል ነው።
አገራቸውን ወክለው በአህጉር አቀፍ ደረጃ ድንቅ ውጤት ያስመዘገቡት ጀግኖች ይህን ሽልማት ያገኙት፤ ከአንድ ግለሰብ አይደለም-ከመንግስት እንጂ።
ዜናውን የሰሙ አስተያዬት ሰጪዎች፦ይህን ሽልማት አሳዛኝ የሚያደርገው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አንድ ላይ በመሆን ያበረከቱት ነው መባሉ ነው ይላሉ።
ማሂ ፋንትሽ ውቤ የተባለች የፌስ ቡክ ተጠቃሚ በ ዎሏ ላይ ባሰፈረችው አስተያዬት፦”በመጀመሪያ ዜናውን ስሰማ ‹‹ከ1000-2000 ሺ ብር ተሸለሙ›› የማለት አዝማሚያ ያለው መስሎኝ በጣም እያዘንኩ ነበር፡፡1000ሺ እና 2000ሺ ብር ምን ታረግላቸዋለች ? በማለት።ሽልማቱ በቦንድ መልክ መሆኑን ስረዳ ደሞ የተሰማኝን እናንተው ጨርሱት”ብላለች።
ሌላው ያስገረማት ነገር የመንግስት ሚዲያዎች ፦”ሉሲዎችን ወክላ በመድረኩ ስትናገር የነበረችው ተጨዋች ሽልማቱ በቀጣይ ለበለጠ ድል እንደሚያነሳሳቸው ተናግራለች”ማለታቸው እንደሆነ የጠቀሰችው ማሂ፤ “ እውን ይህ እውነት ይሆን???”ስትል ትዝብቷን በጥያቄ ቋጭታለች።
በሌላ በኩል በሮም እየተካሄደ ባለው ዲያመንድ ሊግ የ አትሌቲክስ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ አበባ አረጋዊ በ 1500 ሜትር አስደናቂና አስደማሚ ድል ተቀዳጅታለች።
በሚገርም ፍጥነት እየተምዘገዘገች ተከታዮቿን በሙሉ በረዥም ርቀት ጥላቸው ያፈተለችው አበባ አረጋዊ፤ርቀቱን 54 ደቂቃ ከ 56 ነጥብ 54 ሰከንድ በመግባት ለራሷና ለሀገሯ አዲስ ክብረ ወሰን አስገኝታለች።
ተወንጫፊዋ ጠይም እንስት ቀደም ሲል ተይዞ የነበረውን የርቀቱን ሪከርድ ያሻሻለችው በሦስት ሰከንድ ሲሆን፤ይህም ሺህ አምስት መቶን በመሣሰ የጥቂት ደቂቃዎች ሩጫ አስገራሚ ውጤት ሆኖ ተመዝግቧል።
በሮም እየተካሄደ ባለው ጎልደን ሊግ ያልተጠበቁ ወጣቶች ብቅ ብቅ ማለታቸው፤ በቅርቡ በለንደን በሚካሄደው ዓለማቀፍ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ከ እስከዛሬው የተሻለ ሜዳሊያዎችን ታገኛለች የሚለውን ግምት ከፍ ያለ አድርጎታል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide