የሰሜን ጎንደር የመኢኣድ ምክር ቤት የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ ታሰሩ

ግንቦት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በጎንደር ከተማ አደባባይ እየሱስ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ታድሎ ተፈራ የታሰሩት ትናንት ሲሆን፣ ከ10 ያላነሱ ፖሊሶች ወደ ቤታቸው በመሄድ እና ከፍተኛ ፍተሻ በማካሄድ አፍነው ወስደውታል። የበለሳ ተወላጅ የሆነው አቶ ታደሎ ተፈራ  ጎንደር ከተማ ውስጥ ከአክስቱ ጋር ይኖር ነበር። አክስቱ  ወ/ሮ ዘርጊባቸው ሀይሉ ለኢሳት እንደገለጡት ግለሰቡን በርካታ ፖሊሶች ስራ ይሰራበት ከነበረው ደልጊ ከተማ ይዘው በመምጣት ቤቱን ፈትሸዋል::

በደባርቅ አቶ ስለሺ ጥጋቤነህ ፣ በጭልጋ ደግሞ አቶ መለሰ አስሬ  ከትናንት በስቲያ ታፍነው መወሰዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ግለሰቦቹ ታፍነው ስለተወሰዱበት ምክንያት እና የት እንዳሉ የታወቀ ነገር የለም። ይሁን እንጅ ዛሬ ከአቶ መለሰ ቤተሰቦች ባገኘነው መረጃ ግለሰቡ ቤታቸው ሲፈተሽ ምንም ነገር አልተገኘባቸውም። የጭልጋ ነዋሪዎች ድርጊቱን ለመቃወም ሙከራ ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።  መንግስት በግለሰቦቹ መታሰር ዙሪያ የሰጡት አስተያየት የለም።

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ግለሰቦቹ የታሰሩት ከዋልድባ ገዳም እና ከራስ ዳሸን  ጋር በተያያዘ በአካባቢው ከሚታየው ውጥረት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። የደባርቅ ወረዳ ወጣቶች ከዋልድባ፣ ከራስ ደጀን እንዲሁም ከመልካም አስተዳዳርና ፍትህ እጦት ጋር በተያያዘ ከአካባቢው ባለስልጣናት ጋር በተደጋጋሚ እንደሚላተሙ ይታወቃል። የደባርቅ መምህራን የደሞዝ ጭማሪ ይደረግልን በማለት ተቃውሞ ካሰሙ መምህራን መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው። በጭልጋ ወረዳም እንዲሁም መምህራን የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide