መንግስት ዋልድባ ገዳምን ለማፈራረስ የጀመረውን ዘመቻ በመቃወም ሰልፍ ተደረገ

ግንቦት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሜልበርን መድሃኔዓለም ደብር አስተባባሪነት በተጠራው በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ለመገኘት ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ከተሰባሰበ በኋላ ወደ ፓርላማው ህንጻ አምርቷል።

በፓርላማው ጽ/ቤት በመገኘትም  መንግስት አለም አቀፍ እውቅና ያለውን የዋልድባ ገዳም ለማፍረስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም ኢትዮጵያዊ ወገን የሚያደርገውን ጥረት የአውስትራሊያ መንግስት እንዲያግዝ የሚጠይቁ ልዩ ልዩ መፍክሮችን ሲያሰማ አርፍዷል።

በሰልፉ ላይ የተገኙት የሜልበርን መድሃኔአለም ደብር አስተዳዳሪ ሊቀ ካህናት መዘምር ብሩ በዋልድባ ገዳም ላይና በዛም በሚገኙ ቅዱሳን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና በደል በማስታወስ ቃለ ቡራኬ አካፍለዋል።

ሊቀ ካህናት መዘምር በንግግራቸው “ለሃገራችን ሠላም እና ለህዝቦቿ ደህንነት እንዲጸልዩ የምንጠይቃቸው ቅዱሳን አባቶቻችን ዛሬ እራሳቸው መጠለያ እስከ ማጣት መድረሳቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው” ብለዋል።

ሰልፈኛው ይህንኑ የዋልድባ መፈራረስ አስመልክቶ ህጋዊ ሲኖዶስ ለተባበሩት መንግስታት የጻፈውን ደብዳቤ  ለሚመለከተው የመንግስት ባለስልጣን በግልባጭ አስገብቷል። በተሰጠውም ምላሽ የአውስትራሊያ መንግስት ጉዳዩን እንደሚከታተልና የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

በሌላ ዜና ደግሞ ዛሬ ከ16 ያለነሱ በላያቸው ላይ መትረጌስ የተጠመደባቸው ላንድ ክሩዘሮች በደባርቅ ከተማ ላይ እየተዘዋወሩ ህዝቡን ለማስፈራራት ሙከራ አድርገዋል።  ከዋልድባ ገዳም ጋር በተያያዘ በአካባቢው ያለው ውጥረት እየጨመረ መምጣት የፌደራል ፖሊስ አባላት የማስፈራራቱን እርምጃ እንዲወስዱ ሳያደርጋቸው አልቀረም። ባለፈው ሳምንት የደባርቅ ተወላጅ የሆነው አቶ ስለሺ ጥጋቤነህ ታፍኖ መወሰዱ ይታወሳል። ከአንድ ወር በፊትም በተመሳሳይ 25 መትረጌስ የተጠመዱባቸው ላንድ ክሩዘሮች በሰሜን ጎንደር በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች እየተዟዟሩ በህዝቡ ውስጥ ሽብርና ፍርሀት ለመልቀቅ ሲሞክሩ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide