የሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ዛሬም ትምህርት አልጀመሩም

ግንቦት ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሃሮማያ /ዓለማያ/ ዩኒቨርስቲ በቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ ውስጥ የሚገኘው “የወተር ኢንጂነሪንግ” ዲፓርትመንት የአራተኛ ዓመት ተማሪዎች ባነሱት አካዳሚክ ጥያቄ ሳቢያ ፌዴራል ፖሊስ ወደ ዶርማቸው ገብቶ ስለደበደባቸው በርካታ ተማሪዎች ተጎድተዋል፡፡

መብታቸውን የጠየቁ ተማሪዎች ለሁለት ቀናት የመመገቢያ ካርዳቸውን ተነጥቀው ምግብ እንዳያገኙ መደረጋቸውንና ዩኒቨርስቲው ሙሉ በሙሉ በፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ ሥር እንደሚገኝ ተማሪዎች ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎቹ ” በሀገሪቱ ያሉ ሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ይህን የትምህርት ዘርፍ “ሃይድሮሊንክ” በሚል ሥያሜ የሚሰጡ ቢሆንም ለእነሱ ደግሞ ተመሳሳይ ትምህርት እያጠኑ ወተር ኢንጂነሪንግ ተብሎ መሰየሙ በሥራ ዓለም ላይ ያላቸውን ተፈላጊነት በ75 በመቶ እንደቀነሰባቸው ይናገራሉ።

ተማሪዎች ባነሱት አካዳሚክ ጥያቄ ዲፓርትመንቱ ካልፈለጋችሁ ጊቢውን ለቃችሁ ውጡ በማለቱ ጥያቄው ተካሮ ሁሉም የዲፓርትመንቱ ተማሪዎች አንመዘገብም በማለታቸው ባለፈው አርብ የፌዴራል ፖሊስ ዩኒቨርስቲውን ከብቦ ወደ ወስጥ በመዝለቅና ወደ መኖሪያ ግቢያቸው በመግባት በቆመጥ ተማሪዎችን በመደብደቡ በርካታ ተማሪዎች ተፈንክተዋል፣ ተረጋግጠዋል ።

የፌዴራል ፖሊስ አባላት በተማሪ የደህንነት ኋይሎች እየተመሩ  ከሁለተኛ እስከ አምስተኛ ዓመት የደረሱ የዲፓርትመንቱ ተማሪዎች ወደ ሚገኙበት ክፍል በመግባት በቆመጥ በመቀጥቀጥና በማንበርከክ የመመገቢያ ካርዳቸውን ነጥቀው ለሁለት ቀናት አስርበዋቸዋል። ወደ ውጭ ወጥተው የነበሩ ተማሪዎችንም ከውጭ የከበቡት ፖሊሶች አላስገባ ብለው ውጭ አሳድረዋቸዋል ፡፡

ከሰዓት በኋላ  ተማሪዎች በሁኔታው ተቆጥተው ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን፣ ፖለቲካዊ አቅጣጫ እንዳይዝ በመፍራት ፌዴራል ፖሊስ ጊቢውን ተቆጣጥሮታል። ተማሪዎች ወደ ትምህርት ሚንስቴር ለማምራት በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዛሬው እለትም ትምህርት አለመጀመራቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide