በአቶ መለስ ዜናዊ ላይ የተደረገው ተቃውሞ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት ስቧል

ግንቦት ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንግዶች ሆነው ወደ አሜሪካ ከተጓዙት የአፍሪካ መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ መለስ ከፍተኛ ተቃውሞ በማስተናገድ በኩል ብቸኛው መሪ ናቸው። የጋና ፣ የታንዛኒያና የቤኒን መሪዎች ያለምንም ተቃውሞ ተልእኮዋቸውን ሲያሳኩ፣ አቶ መለስ ዜናዊ ከጉባኤ አዳራሽ ውጭ ብቻ ሳይሆን ባልጠበቁት ሁኔታ በአዳራሹ ውስጥ የገጠማቸው ተቃውሞ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀንን ትኩረት ስቧል።

በአውሮፓ ውስጥ በተለይም በአውሮፓ ህብረት አባል አገሮች ከፍተኛ ተደማጭነት ያለው ዩሮ ኒውስ የተባለው የመገናኛ ተቋም ባወጣው ዘገባ፣ ከ400 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ምእራባዊያን መንግስታት አምባገነን መንግስታትን ለማስወገድ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይገባቸው እንደነበር መናገራቸውን ገልጧል። ዩሮ ኒውስ የማርች ፎር ፍሪደም አስተባባሪ የሆኑትን ዶ/ር ካሳ አያሌውን ጠቅሶ እንደዘገበው “ የተቃውሞው ዋና አላማ በምእራባዊያን እርዳታ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰፈነው አምባገነንነትና የጦር ወንጀል እንዲቆም ለመጠየቅ ነው።” የዩሮ ኒውሱ ዘጋቢ ስቴፋን ግሩቤ እንዳለው “ አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች በጉባኤው ላይ እንዲካፈሉ መጋበዛቸው እና እነሱን ለመቃወም የወጡት የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የሰጡት ድምቀት ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ትክክለኛ የቡድን 8 አገሮች ስብሰባ እየተካሄደ እንደሆነ እንዲሰማቸው አድርጓል” ብሎአል።

ዋሽንግተን ፖስት ባወጣው ዘገባ  ደግሞ ኢትዮጵያውያን ያሰሙት ተቃውሞ በሜሪላንድ የሚኖሩ ዜጎችን ትኩረት በእጅጉ ስቧል። ዋሽንግተን ፖስት ሰልፈኞቹ “አሳፋሪ፣ ጨካኝ አምባገነን፣ ውሸታም፣ ጨፍጫፊ መሪ” የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ ሲያወግዙ እንደነበር ገልጧል።

ቼሪ ማገርስ የተባለች አሜሪካዊት በኢትዮጵያኑ የተቃውሞ ሰልፍ መገረሙዋን ገልጣ፣ በዚህ የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ ለመሳተፍ መምጣቱን ተናግራለች።

አቢሲ 2 የተባለው የዜና ማሰራጫም በበኩሉ በ3 አውቶቡስ የተጫኑ ኢትዮጵያውያን የአገራቸውን ሰንደቅ አላማ እያውለበለቡ በባልቲሞር አካባቢ በመገኘት መለስ ዜናዊ የሚያደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት  ተቃውመዋል። ሄራልድ ሜል የተባለው ድረገጽም እንዲሁ አቶ መለስ ዜናዊ በአለማችን ካሉ በሰብአዊ መብት ጥሰት ከሚታወቁት መካከል ግንባር ቀደሙ ናቸው ካለ በሁዋላ፣ በኦጋዴን የተፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አትቷል። ጋዜቴ ኔት የተባለው ድረገጽ በበኩሉ ተቃውሞው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸመውን  የጅምላ ግድያ ለአለም ለማሳወቅ መዘጋጀቱን ጠቁሟል።

የገዢው ፓርቲ ልሳናት እና የመንግስት የመገናኛ ብዙሀን አነስተኛ ሽፋን የሰጡት የዘንድሮው የቡድን ስምንት ጉባኤ ለአቶ መለስ  እና በውጭ ላሉ ደጋፊዎቻቸው ታላቅ ሽንፈት ፣  እርሳቸውን ለሚቃወሙት ሀይሎች ግን ታላቅ ድል ተደርጎ ተቆጥሯል። አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሲሾሙ፣ በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ከተቻለ ደጋፊ ካልተቻለ ተቃዋሚ እንዳይሆን የማድረግ ስትራቴጂ ለመከተል ወስነው ሲንቀሳቀሱ ነበር። ይሁን እንጅ በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ በአቶ መለስ አገዛዝ ላይ የሚሰማው ተቃውሞ እየጨመረ መሄዱን ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አሁንም ለኢሳትና ለጋዜጠኛ አበበ ገላው ያላቸውን አድናቆት እየገለጡ ነው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide