ጋዜጠኛ አበበ ገላው በአቶ መለስ ዜናዊ ላይ ያሰማው ተቃውሞ የኢትዮጵያውያን መነጋገሪያ መሆኑን ቀጥሎአል

ግንቦት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባጠናቀረው ዘገባ እንዳመለከተው መንግስት የአበበ ተቃውሞ እንዳይሰማ የኢንተርኔት ስርጭቶችን ቢዘጋም  አስቀድመው ቪዲዮውን ያገኙ ኢትዮጵያውያን በሞባይል ስልክ ሳይቀር እየተቀባበሉት ነው። አንዳንድ ደፋሮች ለስልካቸው መጥሪያ እየተጠቀሙበት ነው ብሎአል።
የከተማው ታላቁ የመወያያ ርእስ  የአበበ ድርጊት መሆኑን የገለጠው ዘጋቢያችን ፣ ገዢው ፓርቲ መልእክቱ እንዳይሰራጭ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካላትም ብሎአል።
በሌላ በኩል ደግሞ የገዢው ፓርቲ  የመገናኛ ብዙሀን የአበበን ተቃውሞ እያወገዙ ነው። የቀድሞዋ የአሜሪካ ደምጽ ጋዜጠኛ የአሁኑዋ የዛሚ ኮምኒኬሽን ባለቤት የሆነችው ሚሚ ስብሀቱ የአበበን ድርጊት በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት አጼ ሀይለስላሴን ከተቃወሙት የጣሊያን ጋዜጠኞች ጋር አመሳስላ መናገሩዋ ተሰምቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ዲና ሙፍቲ ፍኖተ ነጻነት ላቀረበላቸው ጥያቄ እንዲህ አይነት ነገር ስለመፈጸሙመረጃ እንዳልደረሳቸው ሲገልጡ፣ አቶ በረከት ስምኦን ደግሞ እንዲህ አይነት ነገር ያጋጥማል ብለዋል። ከፍተኛ ተቃውሞአቸውን የገለጡት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ግርማ ብሩ ሲሆኑ፣ አቶ ግርማ አበበን ጋዜጠኛ ሳይሆን ፖለቲከኛ ነው ብለዋል።
በአገር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አበበን ብሄራዊ ጀግና ማድረግ መጀመራቸውና የትግል ስሜታቸውን እንደቀሰቀሰላቸው  በስፋት እየገለጡ ባለበት በዚህ ወቅት የመንግስት ደጋፊዎች በአበበ ላይ የጀመሩት ዘመቻ መንግስት በድርጊቱ  እጅግ  መበሳጨቱን ያሳያል ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide