ሚያዚያ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-አንድነት ፓርቲ ዛሬ ሚያዚያ 26፣ 2004 ዓም በወላይታ ሶዶ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ መጥራቱን ተከትሎ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች በሰብሳቢዎቹና በተሰብሳቢዎቹ ላይ ከፍተኛ ወከባ አድርሰዋል። በስብሰባው ላይ ለመገኘት ከአዲስ አበባ ወደ ወላይታ ያመሩት ኢ/ር ዘለቀ ረዲ፣ ዶ/ር ሀይሉ አርአያና አቶ ዳንኤል ሺበሺ ወደ ከተማዋ ሲገቡ መኪናቸው ጉዳት እንደደረሰባት፣ እንዲሁም ደጋፊዎቻቸውና የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ ስብሰባ አዳራሹ እንዳይሄዱ ክልከላ እንደተደረገባቸው የደቡብ ክልል የአንድነት ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ በስፍራው ለተገኘው ዘጋቢያችን ገልጠዋል
የአካባቢው ባለስልጣናት ያደረሱትን ጫና ተቋቁመው የተገኙ ነዋሪዎች ሰላማዊ ትግል የሚያስከፍለውን ጉዳት በመዘርዘር ንግግር አድርገዋል። መሪዎች ከፍተኛ የሆነ መስዋትነት መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ያወሱ አንድ ተናጋሪ ፣ ነጻነት በትግል እንጅ በስጦታ እንዳማይገኝ ተናግረዋል።
የፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ተመስገን ዘውዴ ደግሞ ነጻ ህዝብ ብቻ ነው በኢኮኖሚ ሊያድግ የሚችለው በማለት የኢህአዴግን የኢኮኖሚ እድገት ፕሮፓጋንዳ ውድቅ አድርገዋል
የስብሰባው መሪዎች ንግግራቸውን ካቀረቡ በሁዋላ የኢህአዴግ ተወካዮች መድረኩን ለመበጥበጥ ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር በስፍራው የተገኘው ዘጋቢአችን ገልጧል።
አንድነት ፓርቲ በደቡብ ክልል ተመሳሳይ ስብሰባዎችን ለማድረግ እቅዶችን መዘርጋቱን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide