በደሴ ከተማ ከጁምአ ጸሎት በሁዋላ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሄደ

ሚያዚያ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-በደሴ ከተማ  በፉርቃን መስጊድ ለአምስተኛ ጊዜ የተካሄደው ይህ የተቃውሞ ሰልፍ  በድምቀቱም ሆነ  በህዝብ ብዛት  ባለፉት አራት ሳምንታት ከተካሄዱት ሰልፎች የበለጠ  ሆኖ ታይቷል።

የሰልፉ አስተባባሪዎች መንግስት  በብዙሀን ሙስሊሞች ላይ ያነጣጠረ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ባስተላለፈበት ጊዜ  የተካሄደው ሰልፍ  ይበልጥ ጠንካራ እና ደማቅ የሆነው፤ ህዝበ-ሙስሊሙ  መንግስት  የቀረበለትን የመብት ጥያቄ  በሀይል ለመፍታት በያዘው መንገድ   ላይ  ይበልጥ እየተቆጣ ስለመጣ ነው ብለዋል።

በተለይ ባለፈው ሳምንት በ አርሲ አሰሳ  የፌዴራል ፖሊሶች መስጊድ ውስጥ በመግባት  በሙስሊም ሰልፈኞች ላይ ተኩስ በመልቀቅ በርካቶችን መግደላቸውና ማቁሰላቸው ከተሰማ ወዲህ ሙስሊሙም ሆነ ክርስቲያኑ የከተማው ህዝብ ክፉኛ መቆጣቱን በስፍራው ለሚገኘው የኢሳት ዘጋቢ  አስተባባሪዎቹን በማነጋገር ያጠናቀረው መረጃ ያመለክታል።

“ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል” እንዲሉ መንግስት  ይባስ ብሎ ሰሞኑን በጁምአ ዋዜማ በራዲዮ እና በቴሌቪዥኑ  ያልተባለውን ነገር ሁሉ እየጠመዘዘ  ሲዝትብን እና ሲያስፈራራን ውሎ ማምሸቱ እጅግ አስቆጥቶናል ያሉት  ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የሰልፉ አስተባባሪ፤ “ለማስፈራሪያ መግለጫውም፤ለጥይቱም እንደማንንበረከክ፤ ደማቅ ሰልፍ በማድረግ ምላሽ ሰጥተነዋል”ብለዋል።

ሙስሊሙ ህብረተሰብ ያነሳቸው የመብት ጥያቄዎች ቀጥተኛ እና ተገቢ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ የተቃውሞ ሰልፉ በቀጣዮቹም ሳምንታት  ይበልጥ በተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስተባባሪው አስታውቀዋል።

እጅግ በርካታ ፖሊሶች የመስጊዱን ዙሪያ በመክበብ   በአርሲ-አሰሳ  እንዳደረጉት ሁሉ  ሰልፈኛው ላይ ለመተኮስ ቢቋምጡም፤ ፍፁም ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሞውን ሲያሰማ የነበረው ህዝበ-ሙስሊሙ አንዳችም ምክንያትና ቀዳዳ ሊከፍትላቸው ስላልቻለ፤ግጭት አለመከሰቱንም አስተባባሪው ተናግረዋል

በአዲስ አበባ መርካቶ አንዋር መስኪድ ከስድስት መቶ ሺህ ህዝብ በላይ በመስኪድ ውስጥና በአካባቢው የተሰባሰቡ ሲሆን ከእስከዛሬው በጠነከረና በተዋቀረ መልኩ መፈክሮችን በጽሑፍና የመጅሊስ አባላትን ፎቶ በተዘቀዘቀ ምስል ይዘው እየቀደዱና እየረገጡ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ መዋላቸውን መዘገባችን ይታወቃል።

ዘጋቢያችን ያናገራቸው አንድ ሽማግሌ ከኮልፌ ወደ አንዋር መስኪድ ተቃውሟቸውን ለመግለጽ መምጣታቸውን ገልጸው በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት /ኢቲቪ/ በኩል የሀሰትና የውሸት መግለጫ የሰጠው የኢህአዴግ መንግሥት ድርጊት በእልክ እንዲወጡ እንዳደረጋቸውና በርካታ ሙስሊኖችም ድምፃቸውን ለማሰማት ዛሬ በተለይ ወደ መስኪድ መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ሙስሊሙን ማህበረሰብ ልክ እንደ ነጋዴው፣ የመንግሥት ሠራተኛው፣ መምህሩ ሁሉ ንቆታል ያሉት እኚህ ሽማግሌ፣  ለዚህም ነው በትላንትናው የማስፈራሪያ መግለጫው ላይ የመብት ጩኸታችን ውስጥ የውጭ ኃይሎች፣ ታጣቂዎች፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች እና ሌሎች ጸረ ሰላም ኃይሎች እንዳሉበት አድርጎ ትግላችንን ሊቀለብስ ሞክሯል ብለዋል፡፡

ዘጋቢያችን በሥፍራው ተንቀሳቅሶ እንደተመለከተው ሙስሊሙ ማህበረሰብ እራሱን በተዋቀረና በሠላማዊ መንገድ ተቃውሞን እንዳስተጋባ፣ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ደግሞ ከራጉኤል ቤተክርስቲያን አቅራቢያ ተከማችቶ ተመልክቷል፡፡

ዘጋቢያችን ያናገራቸው አንድ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጊዜያዊ ተወካይ እንደገለጹት ዛሬ በየመስኪዱ ሙስሊሙ ተቃውሞውን ቢያሰማም አንድም ድንጋይ አልተወረወረም፣ ረብሻም አልተፈጠረም፤ ፖሊሶች ግን ትንኮሳ ሊያደርጉ ቀርበውን ነበር ብለዋል፡፡

ከፍተኛ የሆነ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በመላ አገሪቱ በሚገኙ ዋና ዋና ከተሞች ተሰማርተው እንደሚገኙ ዘጋቢዎቻችን ገልጠዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide