የአፍሪካ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የሚፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አወገዘ

ሚያዚያ ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈጸሙትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች አንድ በአንድ በመዘርዝር፣ የመለስ መንግስት አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።

የአፍሪካ የሰብአዊ እና የህዝቦች መብቶች ኮሚሽን በጋምቢያ ዋና ከተማ በባንጁል ከኤፕሪል 18 እስከ ሜይ 2 ባደረገው ስብሰባ ላይ ባወጣው የአቋም መግለጫ በኢትዮጵያ ውስጥ እስረኞች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ አሰቃቂ ድብደባዎች  (ቶርቸር) ይፈጸምባቸዋል ብሎአል።

እስረኞች ነጻ ታዛቢዎችን ፣ የህግ አማካሪዎቻቸውን፣ ጎብኝዎችንና ቤተሰቦቻቸውን ለማግኘት ችግር እንዳለባቸው ገልጠዋል። በመግለጫው በአገሪቱ ውስጥ ወታደራዊ ካምፖችን ጨምሮ በተለያዩ የማይታወቁ ቦታዎች ዜጎች እንደሚታሰሩ ተገልጧል። ጋዜጠኖችን እና ፖለቲከኞችን በአሸባሪነት እና በአገር ክዳት ስም ማሰር መቀጠሉ እጅግ እንዳሳሰበው ገልጦ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶችን  ለመዝጋት ተብሎ የተረቀቀውን ህግ ኮንኗል።

ኮሚሽኑ የመለስ መንግስት  ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብር፣ በእስር ላይ የሚገኙት ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከህግ አማካሪዎቻቸው እና ከጎብኝዎቻቸው ጋር እንዲገናኙ፤ ስውር እስር ቤቶች እንዲዘጉ፣ አለማቀፍ መስፈርቶችን  የሚያሟሉ ነጻ ፍርድ ቤቶች እንዲቋቋሙ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ደርጅቶችን ለመቆጣጠር ተብሎ የተረቀቀው ህግ እንዲሻሻል፣ እንዲሁም ሀሳብን የመግለጽን መብቶች የሚያፍኑት የኢንፎርሜሽን ህግና የጸረ ሽብርተኝነት ህጎች እንዲሰረዙ ጠይቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide