ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ እየተጉላላ ነው

ሚያዚያ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም  

ኢሳት ዜና:-በወጣቶች እና በምሁራን  የተቋቋመው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ በርካታ አባላትን ምፍራቱ የሚነገርለት ሰማያዊ ፓርቲ ፤ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ ፈቃድ ማግኘት እንዳልቻለ ገለጸ።

ሰማያዊ ፓርቲ  የተቋቋመው የዛሬ አምስት ወር አካባቢ ቢሆንም፤ አባላት ከማፍራት ጀምሮ በ አጭር ጊዜ ውስጥ እያደረጋቸው ያሉት እንቅስቃሴዎች  በመንግስት ዘንድ  ስጋት ማሳደር ሳይጀምሩ እንዳልቀሩ አንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ጠቁመዋል።

የተለያዬ ምክንያቶችን በመፍጠር ምርጫ ቦርድ የፈቃድ ጥያቄውን እያጓተተው ያለውም፤የፓርቲውን ፈጣን  የሆነ ጅምር እንቅስቃሴ ለመግታት በማሰብ ነው ብለው እንደሚያምኑ አመራሩ ለኢሳት ወኪል ተናግረዋል።

ለዚህም ይመስላል ከተቋቋመ ገና  አምስት ወራት የሆነው ሰማያዊ ፓርቲ፤ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለአገሪቷ ሕግና ደንብ ተገዢ ሊሆን ይገባዋል ሲል አሣስቧል፡፡

 በአገሪቷ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ለመካተት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ  ያመለከተው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ሕጋዊ ሰውነቱን የሚያረጋግጥለትን ሰርተፊኬት ለማግኘት ከምርጫ ቦርድ ጋር መስማማት እንዳልቻለ  አስታውቋል፡፡

የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አሮን ሰይፉ፣ ሰማያዊ ፓርቲ ሕጋዊ ሰውነት ሊያሰጠው የሚያስችለውን ፎርማሊቲ በሙሉ አሟልቶ ለቦርዱ የምዝገባ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ቦርዱ ሰርተፊኬቱን ለፓርቲው ሊሰጠው ፈቃደኛ ብለዋል።

ፓርቲያቸው ጥር 19 ቀን 2004 ዓ.ም. ሕጋዊ ሰውነት እንዲያገኝ የሚያትተውን ማመልከቻ ለምርጫ ቦርድ ቢያስገባም፤ እስካሁን ድረስ ቦርዱ ምላሽ ባለመስጠቱ ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነት ሊያገኝ እንዳልቻለ የገለጹት  አቶ አሮን፣ የፖለቲካ ፓርቲው ማመልከቻውን ለምርጫ ቦርድ ካቀረበ ሦስት ወራት ማለፋቸውን አብራርተዋል፡፡

“በሕጉ መሠረት ፓርቲው እንደተመዘገበ  ቢቆጠርም፤ ሕጋዊ ሰውነቱ ግን ሊረጋገጥ አልቻለም፤›› ሲሉ በምሬት የተናገሩት አቶ አሮን፤ሕጋዊ ሰውነቱን ካላገኘ ደግሞ  ማንኛውንም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

 በዚህም ምክንያት ፓርቲው ለተለያዩ ዓላማዎች አዳራሽ መከራየትም ሆነ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት መክፈት እንዳልቻለ በመግለጫው አመልክቷል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide