የአሶሳ ሚሊኒየም ፓርክ በእሳት ቃጠሎ ወደመ

ሚያዚያ ፲፩ (አስራ አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኘው የአሶሳ ሚሊኒየም ፓርክ ሰሞኑን በደረሰበት የ እሳት ቃጠሎ ሙሉ በሙሉ ወደመ።
መንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የአሶሳን ፖሊስ ጠቅሶ እንደዘገበው፤ የአሶሳን ሚሊኒየም ፓርክ ሙሉ ለሙሉ ላወደመው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ አንድ አርሶ አደር በቁጥጥር ሥር ውሏል።
መንግስት ፤የእሳት ቃጠሎው የተነሳው በፓርኩ አቅራቢያ የሚገኘው ይኸው አርሶአደር የእርሻ ማሳውን ለማፅዳት የለኮሰው እሳት ወደ ፓርኩ በመዛመቱ ነው ባይ ነው።
ይሁንና ይህ የአሶሳ ፖሊስ ሪፖርትና እና የመንግስት ምክንያት በሌላ ገለልተኛ አካል አልተረጋገጠም።
በአደጋው የወደመው ፓርክ ከከተማው አቅራቢያ ከ2000 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ተከልሎ የለማና 150 ሔክታር መሬት ያህል ስፋት እንዳለው ተመልክቷል።
በእሳት አደጋው ከፓርኩ በተጨማሪ በአቅራቢያው የሚገኙ ስድስት መኖሪያ ቤቶችም ተቃጥለዋል::
የከተማው ነዋሪዎች ከአካባቢው ፖሊሶች ጋር በመተባበር ባደረጉት ርብርብ እሳቱ ወደ ከተማው ሳይዛመት ሊጠፋ መቻሉ ተገልጿል::
አሶሳ ሚሊኒየም ፓርክ፤ በቀርከሃ፣ በዋንዛ፣ በግራር፣ በሳርና በሌሎች ዕፅዋቶች የተሸፈነ ጥቅጥቅ ያለ ደን የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ በእሳት ወድሞ ራቁቱን ይታያል።
አቶ መለስ በሰሞኑ የፓርላማ ንግግራቸው የቤንሻንጉል ጉሙዝ መሬት ባለቤት የሌለው ሆኗል በማለት መናገራቸው ይታወሳል። በክልሉ ያለው ደን በከፍተኛ ደረጃ እየወደመ መሆኑን በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል።
_____________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide