መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከመካከላቸው ሰባ የሚሆኑት በመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ጽህፈት ቤት ውስጥ የተጠለሉ ሢሆን፤ብዙዎቹ ተፈናቃዮች ግን ወደ አዲስ አበባ ቢመጡም መጠለያ አጥተው እየተንከራተቱ መሆናቸውን መኢአድ አስታውቋል።
የመኢአድ ዋና ፀሀፊ አቶ ተስፋዬ ታሪኩ እንዳሉት፤ ከቤንች ማጅ ዞን ጉራ ፋርድ ወረዳ ቤትና ንብረታቸውን ጥለው የተሰደዱት እነዚህ ወገኖች አዲስ አበባ በሚገኘው የቅድስት ሥላሴ ቤተ-ክርስቲያን ለመጠለል ቢሞክሩም በጥበቃ ሠራተኞቹ ተከልክለዋል።
ከ 22 ሺህ የሚበልጡት የአማራ ተወላጆች ምትክ ቦታ ሳይዘጋጅላቸው ከይዞታቸው እንዲነሱ በመደረጉ አዲስ አበባ መጥተው ሜዳ ላይ መውደቃቸውን የጠቆሙት ዋና ጸሀፊው፤ ከይዞታቸው እንዲነሱ የተደረጉትም በድንገት ስለሆነ ለዓመታት ያፈሩትን ንብረታቸውን በትነው፣በጎቻቸውንና ፍየሎቻቸውን ትተውና 7 ሺህ ብር የሚያወጣ በሬ በ 1 ሺህ ብር እየሸጡ መሰደዳቸውን ተናግረዋል።
“በአንድ አገር ዜጐች ላይ እንደዚህ ዓይነት በደል መፈጸም፤ በትውልድ መካከል ቂምና ቁርሾ ይፈጥራል” ሲሉ ዋና ጸሀፊው ዕርምጃውን ኮንነዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ከይዞታቸው እንዲለቁ ሲገደዱ በእጃቸው የነበረውን ጥቂት ገንዘብ በሕክምናና በትራንስፖርት ወጪ የጨረሱ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፣ መኢአድ እነኚህን ተጐጂዎች የመርዳት አቅም ስለሌለው በዕርዳታ ላይ የተሰማሩ አካላት መሄጃ ላጡት ለእነኚህ ወገኖች ምግብና መጠለያ የሚሰጡበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጥሪ ማቅረባቸውን የሪፖርተር ዘገባ ያመለክታል።
በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ምትክ ቦታ ሳይዘጋጅላቸው ከይዞታቸው እየተፈናቀሉ ሜዳ ላይ የሚወድቁ ዜጎች ቁጥር በ አስደንጋጭ ሁኔታ እያሻቀበ መምጣቱን በርካታ መረጃዎች ያመለክታሉ።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide