ኢትዮጵያዊ ወጣት ከ 21 ኛ ፎቅ ላይ ራሷን መወርወሯ ተዘገበ

መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ሻርጃህ ውስጥ በቤት ሠራተኝነት ተቀጥራ ታገለግል የነበረች  የ 23 ዓመት ኢትዮጵያዊ ወጣት ከ 21 ኛ ፎቅ ላይ ራሷን መወርወሯን ሻርጃህ ታይምስ ዘገበ።

በሻርጃህ ፖሊስ የሞራልና  የምክር አገልግሎት ዲፓርትመንት  ዳይሬክተር ማጆር መሀመድ ሰኢድ አልሸሂ እንደገለጹት፤ በአረብ ቤተሰብ ውስጥ ትሠራ የነበረችው  ኢትዮጵያዊት ወጣት ራሷን ከምትሠራበት ፎቅ ቤት ላይ በወርወር  ህይወቷን እንዳጠፋች ለሻርጃህ ፖሊስ መረጃው ደርሶታል።

ከፖሊስ የተውጣጣው የወንጀል ምርመራ ቡድን አደጋው የተፈፀመበት ቦታ ሲደርስ ወጣቷን ሞታ እንደተገኘች ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የሟቿ  ወጣት አስከሬን በመጀመሪያ ወደ ኩዌት ሆስፒታል መወሰዱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ከዚያም ለተጨማሪ የፎረንሲክ ምርመራ ወደ  ፖሊስ ላቦራቶሪ መዛወሩን አመልክተዋል።

ከቅርብ ጊዚ ወዲህ በሻርጃህ በተመሣሳይ  መንገድ ራስን የማጥፋት ድርጊቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ሊባኖስ ውስጥ በአሠሪዎቿ  በአደባባይ ላይ እየተጎተተች ስትንገላታ የታየችው ዓለም ደቻሳ ፤ሆስፒታል ከገባች በሁዋላ ራሷን እንዳጠፋች የተነገረው ከሳምንት በፊት ነበር።

ሥራ ፍለጋ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በሚሄዱ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ላይ በአሠሪዎቻቸው አማካይነት እየተፈፀመባቸው ያለው ግፍ እየተባባሰ መምጣቱ የዓለማቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት እየሳበ መምጣቱ ይታወቃል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide