የመምህራን ውዝግብ ዛሬም አልበረደም

መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ የሚገኙ የአንደኛ ደረጃ፣ የሁለተኛ ደረጃ እና የመሠናዶ ትምህርት መምህራን ሰኞ ወደ ማስተማር ተግባራቸው ከመመለሳቸው በፊት በየትምህርት ቤታቸው እንዲሰባሰቡና በግላቸው ተወያይተው የአቋም መግለጫ በማውጣት ለትምህርት ቤቱ አስተዳደር፣ ለየወረዳ፣ ክፍለ ከተማ እና የአዲስ አበባ መስተዳደር ትምህርት ቢሮ እንዲያስገቡ ጥሪ እያስተላለፉ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ከአስተዳደሩ እውቅና ውጪ የሚደረጉ ስብሰባዎች ሁሉ ሕገወጥ ናቸው ብሏል፡፡

 ትናንት ለመምህራን በስልክ፣ በበራሪ ወረቀት፣ በፌስቡክ እና በግል የግንኙነት መረብና በየትምህርት ቤቱ ክበባት የቀረበው ጥያቄ የኢህአዴግ መንግሥት ሰኞ የተመረጡ በመብት ጥያቄው ላይ ከፊት የቆሙ መምህራንን እንደሚመታ፣ እንደሚከፋፍለን እና የተወሰኑትን እንደሚያባርር መረጃ ስለተገኘ ተነጋግረን በተናጥል እንዳንጠቃ ማድረግ አለብን ያሉን ሥማቸውን መግለጽ ያልፈቀዱ የመምህራን ተወካዮች መምህራን ማህበሩ የኢህአዴግ ካድሬ በመሆኑ አይወክለንም ሲሉ ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡

 በአቋም መግለጫችን ላይም አንድም መምህር ሰብያዊ እና ሕገመንግሥታዊ መብቱን ስለጠየቀ ከሥራ መባረር እንደሌለበት፣ ያነሳነውን የደመወዝ ጭማሪ ጥያቄ መንግሥት በተወሰነ ጊዜ መልስ እንደሚሰጠን ማረጋገጫ ካልሰጠን በስተቀር እንደገና ረዘም ያለ የሥራ ማቆም አድማ እንደምናደርግ ማሳወቅ አለብን በማለት የጥሪ መልዕክታቸው ይገልጻል፡፡

 ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ሃሙስና ዓርብ በትምህርት የሥራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ  መምህራን ሥም ዝርዝር በየትምህርት ቤቱ ቦርድ ላይ ለጥፎ ከሰኞ ጀምሮ የማትገኙ ከሆነ በራሳችሁ ፈቃድ ሥራችሁን እንደለቀቃችሁ ተቆጥሮ መንግሥት ሌሎች መምህራንን ለመቅጠር ይገደዳል ይላል፡፡

 ቅዳሜ በየትምህርት ቤቱ የአስተዳደሮች ሠራተኞች በቦርድ ላይ የተለጠፈው ማስታወቂያ ከእንግዲህ በትምህርት ቤት ቅጥር ጊቢ፣ በክበብ፣ እንዲሁም በክፍል ውስጥ መምህራን ከአስተዳደሩ እውቅና እና ፈቃድ ውጪ መሰብሰብ አትችሉም የሚል መለጠፉን መምህራን ማረጋገጣቸውን ለዘጋቢያችን ገልጸው መምህሩ አንድ አስተዳደራዊ ጥቃት እንዳይፈጸምበት ከወዲሁ አንድ ወጥ አቋም መያዝ እና መዋቀር አለብን ብለዋል፡፡

 ሃሙስ እና ዓርብ በየትምህርት ቤቱ የተገኙ ተማሪዎችን የሰበሰበው የወረዳ የትምህርት ቢሮ ተማሪዎችን ድጋፍ እንዲያደርጉለት ቢጠይቅም ለምን ለመምህራን ትክክለኛ የደመውዝ ጥያቄያቸውን መልሳችሁ በአግባቡ ትምህርት እንድናገኝ አታደርጉንም በማለት ድጋፋቸውን ለመምህራን በማድረጋቸው ስብሰባው መበተኑን ከተማሪዎች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide