የካቲት 27 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት ምንጮች እንደገለጡት የመምህራንን ጥያቄ ያለምንም ፍርሀት ለመንግስት በማቅረባቸው፣ በመምህራን ዘንድ ተወዳጅ የሆኑት አቶ መንግስቱ አህመዴን ለመተካት ምርጫ ተካሂዷል
ምርጫውን የሚያካሂዱት የየወረዳው የመምህራን ተወካዮች የዞን ተወካዮችን፣ የዞን ተወካዮች ደግሞ የክልል ተወካዮችን እንዲመርጡ ከተደረገ በሁዋላ ነው።
የምርጫው ስርአት በስልጣን ላይ ላለው የመለስ አገዛዝ ለድርጅቱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ለመምረጥ ያስችለዋል።
መምህራን በምርጫው ቀጥተኛ ተሳትፎ የማያደርጉ በመሆኑ፣ ገለልተኛ መምህራንን በመሪነት ለማስመረጥ አይቻልም ።
ባለፉት ተከታታይ ሳምንታት ማህበሩ መምህራንን በተደጋጋሚ ስብሰባ በመጥራት አዳዲስ አመራሮችን እንደሚርጡ ለማግባባት ሙከራ ሲያደርግ እንደነበር ኢሳት መዘገቡ ይታወሳል።
በሰሜን ጎንደር፣ በምእራብ ጎጃምና በሰሜን ሸዋ የሚገኙ አንዳንድ መምህራን መንግስት በማህበሩ ላይ በሚያሳርፈው ጫና ባለመደሰት ራሳቸውን ከማህበሩ አግልለዋል።
አንዳንድ የማህበሩ አባላት ለማህበሩ ስራ ማስኪያጃ እየተባለ በየወሩ የሚቆረጠው ገንዘብ፣ ከእንግዲህ ያለፍላጎታቸው እንዳይቆረጥ ጠይቀዋል።
መምህር መንግስቱ በአገር አቀፉ የመምህራን ማህበር ጉበኤ ላይ የመምህራንን የደሞዝ ጭማሪ፣ የደረጃ እድገትና የማስተማርና ሀሳብን የመግለጽ፣ ከሁሉም በላይ መምህራን ከፖለቲካ ተጽእኖ ነጻ እንዲሆኑ፣ በሰላማዊ ሰልፍ ሳይቀር መብታቸውን እንዲጠይቁ ሊፈቀድላቸው ይገባል የሚል ሀሳብ መሰንዘራቸውን መዘገባችን ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ 6 የደምቢያ መምህራን የስራ ማቆም አድማ በማድረግ የደሞዝ ጥያቄ ጠይቃችሁዋል ተብለው መታሰራቸውን ተከትሎ በመንግስትና ባለስልጣናትና በተማሪዎች መካከል ውዝግብ ተፈጥሯል፤ ውዝግቡን ተከትሎም ትምህርት ቤት ተዘግቷል።
የወረዳው ባለስልጣናት መምህራኑን ካሰሩ በሁዋላ አዳዲስ መምህራንን ከተለያዩ ቦታዎች በማስመጣት ለመተካት ሙከራ ሲያደርጉ ተማሪዎች፣ የታሰሩት መምህራን የመብት ጥያቄ አነሱ እንጅ ያጠፉት ጥፋት የለም፣ ስለዚህም እነሱ ካልተፈቱ እና ወደ ስራቸው ካልተመለሱ በአዲሶቹ መምህራን አንማርም ማለታቸውን ከአካባቢው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ተማሪዎቹ የያዙት አቋም ያስደነገጣቸው ባለስልጣናቱ፣ መምህራኑን በይቅርታ ለመፍታት ዳር ዳር እያሉ ነው ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በተመሳሳይ መልኩ የደሞዝ ጭማሪ በመጠየቃቸው ከስራ ታግደው ከነበሩት 40 የደባርቅ መምህራን መካከል አስሩ ብቻ ተመርጠው የይቅርታ ፎርም እንዲሞሉ ተደርጓል።
አድማውን መርተዋል የተባሉ መምህራን ይቅርታ እንዲጠይቁ ሲጠየቁ፣ ” መብታችንን ተጠቅመን ጥያቄ በማቅረባችን ይቅርታ አንጠይቅም፣ የስራ መልቀቂያችንን ስጡንና ስራ እናፈላልጋለን የሚል” መልስ ሰጥተው ነበር። የወረዳው ባለስልጣናትም ፤ የስራ መልቀቂያ እንኳን ለማግኘት በቅድሚያ ይቅርታ መጠየቅ አለባችሁ የሚል አቋም በማንጸባረቃቸው፣ መምህራን ሳይወዱ በግድ በአንድ ወረቀት ላይ እንዲፈርሙ ተደርጓል።
አንድ መምህር ” ስራችን ለመጀመር ወይም ስራችንን ለመልቀቅ በማንችልበት አጣብቂኝ ውስጥ ስለከተቱን፣ ‘ከእንግዲህ በተመሳሳይ ድርጊት ብንሳተፍ መንግስት የሚወስድብንን ማንኛውም እርምጃ ለመቀበል ተስማምተናል’ የሚል ራሳችንን የሚወነጅል ሰነድ ፈርመናል በማለት ተናግረዋል።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide