በዋልድባ ገዳም አካባቢ የሚኖሩ አርሶአደሮች ከመንግስት ጋር ተፋጠዋል

የካቲት 27 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዋልድባ ገዳም አካባቢ የሚኖሩ አርሶአደሮች ክልላችንን አናስደፍርም በማለት ከመንግስት ሀይሎች ጋር ተፋጠዋል

ታዋቂውን እና ጥንታዊውን የወልድባ ገዳም ግቢ ለስኳር ምርት በሚል በዶዘር መታረስ መጀመሩን ተከትሎ በርካታ የመነኮሳቱ አጽም ሜዳ ላይ ተበትኖአል። የመንግስት ድርጊት ያበሳጫቸው መነኮሳቱ ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማቅረብ መልስ እናገኛለን ብለው ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ጥያቄ ቢያቀርቡም “እናንተ እነማን ናችሁ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ደፍራችሁ ለማናገር የመጣችሁት” በሚል ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል።

የመንግስት ውሳኔ ያበሳጫቸው የአካባቢው ነዋሪዎች በዚህ ሳምንት ህዝቡ ወጥቶ የገዳሙን ክልል ከመታረስ እንዲከላከል ወረቅት በትነዋል። ጥሪውን የሰሙ በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ ክርስቲያኖች ባላቸው መሳሪያ ሁሉ ለመከላከል ወደ አካባቢው መንቀሳቀስ ሲጀምሩ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች “ለአሁኑ እኛ እንመክታለን፣ ተዘጋችታችሁ ጠብቁ ከእኛ አቅም በላይ ከሆነ እርዳታ እንጠይቅላችሁዋለን” በማለት፣ ሁኔታውን ለማረጋጋት ሞክረዋል።

የአካባቢው አርሶአደሮች በነቂስ በመውጣት አካባቢያቸውን እየጠበቁ መሆኑን ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት  የኢሳት ወኪሎች ገልጠዋል።

የሰሜን ጎንደር ህዝብ መንግስት በወሰደው እርምጃ መበሳጨቱን፣ መንግስትም በአቋሙ ከገፋ ደም መፋሰስ ሊከተል እንደሚችል ወኪሎቻችን አክለው ገልጠዋል።

“በሰበብ አስባቡ መንግስት ህዝቡን ከማበሳጨት አልተቆጠበም፣ አሁን ግን ህዝቡ በቃኝ ማለት የጀመረ ይመስላል፣ ደገኛው በሙሉ ተነቃንቋል ገዳማትን መዳፈር  ካልቆመ የሚፈጠረውን ማን ያውቃል።” በማለት አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አንድ አዛውንት ገልጠዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide