ኮንግረስ ማን ዶናልድ ፔይን ዐረፉ

የካቲት 28 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- “ሰው ማለት፤ሰው የሚሆን ነው ሰው የጠፋ ዕለት” ሲሉ ይሰማሉ-ከሁኔታዎች ጋር ተለዋዋጭ በሆነው በሰው ልጆች ባህርይ- የስሜት ስብራት የደረሰባቸው ወገኖች።

ይሁንና በማህበራዊ ግንኙነትም ሆነ በአገራዊ ፖለቲካው ዙሪያ የጊዜና የሁኔታዎች ግፊት ከያዙት እውነታና አቋም የማያነቃንቋቸው ጥቂት የህሊና ሰዎች አልፎ አልፎም ቢሆን መከሰታቸው አልቀረም።

ከነዚህ ፤ሰው በጠፋ ጊዜ ሰው ሆነው ከተገኙትና በሁኔታዎች ተጽዕኖ ካልተለወጡት መካከል፤  የኢትዮጵያ  የክፉ ቀን ወዳጅ ዶናልድ ፔይን አንዱ ናቸው ይላሉ- አቶ ብሩክ ሰይፈ የተባሉት የሆላንድ ነዋሪ። 

እንደ አቶ ብሩክ ገለፃ፤ ኮንግረስ ማን ዶናልድ ፔይን በብዙሀን ኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ስፍራ አላቸው። በኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን ያለመታከት ደክመዋልና።

ኤች አር 2003 የተሰኘውን የኢትዮጵያ የዲሞክራሲና የተጠያቂነት ህግ ከማርቀቅ አንስቶ፤ ረቂቁ በአሜሪካ ምክር ቤት እስኪያልፍ ድረስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውንም አቶ ብሩክ አስታውሰዋል።

በምርጫ 97 ጊዜ በኢትዮጵያ ብልጭ ብሎ የነበረው የዲሞክራሲ ተስፋ ዳግም እየጨለመ መምጣቱ  በኮንግረስ ማን ፔይን ላይ ከፍተኛ የቁጭት ስሜት ፈጥሮባቸው መቆየቱ ይነገራል።

“በተለይ በምርጫው ማግስት…”በማለት አስተያዬት መስጠት የጀመረው ሌለኛው የሆላንድ ነዋሪ ሀብታሙ ባዩ በበኩሉ ፦” በተለይ በምርጫው ማግስት ገዥው ፓርቲ የተቃዋሚ መሪዎችንና ደጋፊዎቻቸውን አስሮ መንግስት መመስረቱን ባወጀበትና በመንግስት ላይ የሚደረጉት  የውጭ ተፅዕኖዎች ሁሉ  ከሁኔታዎች ጋር እየጠፉ በመጡበት በዛ የፈተናና የሀዘን ጊዜ፤ከተገፉት ብዙሀን ኢትዮጵያውያን ጎን  ከልባቸው የቆሙ ብቸኛ ሰው ናቸው-“ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል- በእውነትና በህሊና መንገዱ ሲያበራ ስለኖረው ስለ ኒው ጀርሲው ጥቁር ክዋክብት ስለ ኮንግረስ ማን  ዶናልድ ፔይን።

ከኢትዮጵያ ባሻገር በምስራቅ አፍሪቃ አስተማማኝ ሰላም የሚመሰረትበትን መንገድ ለመተለም ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት ፔይን ከወራት በፊት፤ ይህን ዓላማቸውን ለማሳካት ወደ ሶማሊያ ባቀኑበት ወቅት “አልሸባብ” በተሰኝው አክራሪ ድርጅት ከተፈፀመባቸው የግድያ ሙከራ ለጥቂት መትረፋቸው ይታወቃል።

 የኒው ጀርሲው ተወካይና የዲሞክራቲክ ፓርቲው  አባል ዶናልድ ፔይን፤   በአንጀት ካንሰር  መታመማቸውን ያወቁት ባለፈው ወር ባደረጉት ምርመራ ነበር።ሆኖም ዶክተራቸው ህመማቸው ሙሉ ለሙሉ ሊድን እንደሚችል ስለነገራቸው በመጪው ምረጫ ለመሳተፍ እቅድ እንደነበራቸው ታውቋል።

የሥራ ባልደረቦቻቸውና የፓርቲያቸው አባላት በቅርቡ ኮንግረስ ማን ፔይን ህክምና በሚከታተሉበት በጆርጅ ታውን ሆስፒታል ተገኝተው ሲጎበኟቸው ግን፤ በጠና ታመው ነው ያገኟቸው።

አንድ ስማቸውን ያልገለጹና ለኒው ጀርሲ ተወካዮች ልዑካን ቅርበት ያላቸው ምንጭ፦“ዶናልድ ፔይን ወደ ህይወታቸው ፍፃሜ በመቃረባቸው የኒው ጀርሲ ተወካይ ልኡኮች አዝነዋል” በማለት  ለ“ካፒቶል”  ብሎግ የነገሩት ከሁለት ቀናት በፊት ነበር።

በጊዜው የፔይን ልጅ  በሰጠው አስተያዬት፦” እኛ ተስፈኞች ነን ። ነገር ግን  ህመሙ  ካንሰር ነው “ ብሎ ነበር።

ይህ ተስፋ ግን ብዙም አልቆየም።ኮንግረስ ማን ዶናልድ ፔይን በተወለዱ በ77 ዓመታቸው  ህክምና ሲከታቱ በነበረበት በኒውጀርሲ- ሊቪንግስቶን በሚገኘው የቅዱስ በርናባስ ሆስፒታል ውስጥ  ማክሰኞ ንጋት ላይ አርፈዋል።

የዶናልድ ፔይን ማረፍ መሰማቱ፤  ከአሜሪካውያን አልፎ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ጭምር ያሳዘነ ሆኗል።

ይህ ለኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ  ፍትሀዊና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን ሆኖ ማየት ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አስደንጋጭና አሳዛኝ ዜና ነው ያሉት አንድ ስማቸውን ያልገለጹ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ፤ ለኛ ፔይንን ማጣት ብዙ ነገር እንደማጣት ነው”ሲሉ ሀዘናቸውን ገልጸዋል።

 የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ለዶናልድ ፔይን ቤተሰቦችና፤ በህልፈታቸው ሀዘን ለበረታባቸው ወገኖች ሁሉ መጽናናት ይሆንላቸው ዘንድ ልባዊ ምኞቱን ይገልፃል።

በተያያዘ ዜና የግንቦት ሰባት የፍትህ፣የነጻነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በሪፐብሊካኑ ተወካይ በኮንግረስ ማን ዶናልድ ፔይን ህልፈት የተሰማውን  ጥልቅ ሀዘን ገልጿል።

“በዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ ውስጥ ጠንካራ ተሟጋችና ተፅዕኖ ፈጣሪ የነበሩት ፔይን በማለፋቸው፤ አሜሪካውያን ታላቅ አርበኛቸውን፤ኢትዮጵያውያን ደግሞ ታላቅ ጓደኛቸውን አጥተዋል” ብሏል-ግንቦት 7 ለኢሳት በላከው መግለጫ።

ዶናልድ ፔይን ለታፈነው የ ኢትዮጵያ ህዘብ ድምጽ እንደነበሩ፣ በአፍሪካና በመላው ዓለም የሰብብዓዊ መብት እንዲከበር፣ዲሞክራሲ እውን እንዲሆንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ  ያለ ድካም ሲታገሉ መቆየታቸውን ንቅናቄው አስታውሷል።

ከካንሰር ህመም ጋር ባደረጉት ጦርነት ታላቅ ድፍረትና ተስፈኝነት የታየባቸውም፤  ገና ረዥም ጊዜ በመኖር  የሰብዓዊ መብቶችን ለማስከበር ከነበራቸው ቁርጠኝነትና ላለፉት 27 ዓመታት ሲያገለግሉት የነበረውን  የአሜሪካና  ኒውጀርሲ ህዝብ በበለጠ ብቃት ለማገልገል  በመፈለጋቸው ብቻ ነው ሲል ገልጿል-ግንቦት 7።

ኤች አር 2003 – “የኢትኦጵያ የዲሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች አዋጅ 2007” ተብሎ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት እስኪያልፍ ድረስ ባሳዩት የመሪነት ሚናም በሚሊዮን የሚቆጠሩ አፍሪካ አሜሪካውያን እንደሚያደንቋቸው የንቅናቄው መግለጫ አውስቷል።

ግንቦት 7 በመጨረሻም በ አባላቱ ስም ባስተላለፈው የሀዘን መልዕክት፦” ዛሬም ሆነ በሚቀጥሉት ቀናት በሀሳብም ሆነ በፀሎት ከፔይን ቤተሰቦች ጋር ነን” በማለት፤

ለቤሰቦቻቸው፣ለጓደኞቻቸው፣ ለአጋሮቻቸውና ይህ የዘመናት  የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በማለፉ ያዘኑ ሁሉ መጽናናት እንደሚሆንላቸው ተስፋውን ገልጿል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide