የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መንግሥትና መጅሊስ እየፈጸመብን ያለው ደባ አሁንም እንደቀጠለ ነው ይላሉ

የካቲት 27 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአቶ መለስ ዜናዊ መንግሥትና በማይወክለን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት /መጅሊስ/ በሃይማኖታችን ላይ እየተፈጸመብን ያለው ደባ አሁንም እንደቀጠለ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አስታወቁ፡፡

በአወሊያ መስኪድ አስተባባሪነት ሕዝበ ሙስሊሙን ወክለው ከመንግሥትና ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት (መጅሊስ) ጋር እንዲደራደሩ የተመረጡት 17 የኮሚቴ አባላት ውይይቱ ፍሬ አልባና ለመንግሥት ያቀረብነው መሠረታዊ ሕገመንግሥታዊ ጥያቄዎች ሁሉ መና ቀርተዋል ብለዋል፡፡

በዛሬው እለት ከመንግሥት በኩል ለጥያቄዎቻችን የመጨረሻ ምላሽ እንደሚሰጡን ገልጸውልን ነበር ያሉት አንድ የኮሚቴው አባል ለስድስት ሰዓታት በተደረገ እልህ አስጨራሽ ውይይት በሚያሳዝን ሁኔታ የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ጥያቄዎች ምላሽ ተነፍገዋል ብለዋል፡፡

መንግሥት በሰጠው ምላሽ መሠረት የመጅሊስ አመራሮች በምርጫ ይተካሉ ያለን ሲሆን ምርጫው በምን አይነት ሁኔታ እንደሚካሄድ፣ በማን በኩል መካሄድ እንደሚገባው እና መቼ እንደሚካሄድ ለጠየቅነው ጥያቄዎችም መልስ አልሰጡንም፣ እንዲያውም አስፈራርተውናል ብለዋል፡፡

የአህባሽን አስተምህሮ በተመለከተ መንግሥት ከአሁን በኋላ ትምህርቱ በግዳጅ አይሰጥም፤ ነገር ግን በመጅሊስ በኩል ትክክለኛ መሆኑ ስለታመነበት አሁንም ቢሆን ትምህርቱን መስጠቱ ይቀጥላል ብለውናል ያሉት የኮሚቴ አባላት የአወሊያ የሃይማኖት ትምህርት ቤት፣ ክሊኒክና መስኪድ አሁን ባለበት ይዞታ በመጅሊስ ሥር ሆኖ ይቀጥላል ሲሉ የፌዴራል ጉዳዮች ሚንሥትር ምላሹን ሰጥቶናል በማለት ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት /መጅሊስ/ አይወክለንም- ይፍረስልን፣ የአህባሽን አስተምህሮ ኢህአዴግ በግድ እየጫነብን ነው- አንቀበለውም በማለት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላለፉት ስምንት ሣምንታት በተጠናከረና በተቀናጀ ሁኔታ ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ፡፡

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide