የደቡብ ክልል ግምገማ ሌሎች ችግሮችን ጥሎ ማለፉ ተነገረ

የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ከየካቲት 19 እስከ 23 ቀን በክልሉ በተካሄደው አራተኛው ዙር አስቸኳይ ጉባኤ  የአዋሳ ከንቲባ የነበሩት  አቶ ሽብቁ መገኔ እንዲታሰሩ ሲወሰን እርሳቸውን ከጀርባ ሆነው ሲደግፉዋቸው በነበሩት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽፈራው ሽጉጤን ላይ ምንም እርምጃ ሳይወስድ ቀርቷል።

ከወራት በፊት በአዋሳ ከተማ በሺ የሚቆጠሩ ቤቶች እንዲፈርሱ በተደረገበት ጊዜ ከንቲባው  ከሌሎች አካባቢዎች የመጡትን ወይም መጤ እያሉ የሚጠሩዋቸውን ነዋሪዎች ቤታቸው እንዲፈርስ ሲያደርግ፣ የሲዳማ ተወላጆችን ቤት ግን እንዳይፈርስ አድርጓል የሚል ክስ በግምገማው ወቅት ቀርቦበት ነበር። ከንቲባው ከጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ መመዝበሩ እንዲሁም በከተማዋ ውስጥ በቤተሰቦቹና በዘመዶቹ ስም በርካታ ቦታዎችን እና ህንጻዎችን መያዙም በግምገማው ወቅት ተነስቷል።

የክልሉ ምክር ቤት አባላት ከንቲባው እንዲታሰሩ በመወሰናቸው ግለሰቡ ከትናንት ጀምሮ ወይኒ መውረዳቸውን ምንጮች ገልጠዋል።

ይሁን እንጅ እርሳቸውን ከጀርባ ሆነው ሲደግፉዋቸውና ሲያበረታቱዋቸው የነበሩት እና በተመሳሳይም በከፍተኛ ሙስና ተዘፍቀው የሚገኙት ፕሬዚዳንቱ  አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ፣ በምክር ቤቱ አባላት ቢገመገሙም ምንም እርምጃ አልተወሰደባቸውም።  አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ ባለስልጣን አቶ ሽፈራውን ከስልጣን ለማውረድ ያልተቻለው ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ባላቸው ግንኙነትና በክልሉ ውስጥ ባለው የብሄረሰብ ችግር ምክንያት ነው ይላሉ።

አቶ ሽፈራው በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማካበታቸውን፣ በክልሉ በቤተሰቦቻቸው እና በዘመዶቻቸው ስም ሰፋፊ ቦታዎችን መያዛቸውን ምንጫችን አክለዋል፡፤

አቶ ሽፈራው ከግምገማው በሁዋላ ማን ነው የሚናገረኝ በማለት እንደሚደነፉ የጠቀሱት ታማኝ ምንጫችን፣ እርሳቸውን የገመገሙዋቸው ሰዎች ሳይቀሩ ይቅር ይበሉን በማለት እየተለማመጡ እንደሚገኙ ገልጠዋል።

የአዋሳ ከተማ ከንቲባ እንዳይታሰሩ ሲከራከሩ ቆዩት አቶ ሽፈራው፣ ግለሰቡ እንዲታሰሩ የተስማሙት የህዝቡን ቁጣ ለማብረድ ሲባል ለጊዜው መሆኑንም አክለዋል።

አቶ ሽፈራው ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በመርዝ የእድሜ ልክ በሽተኛ የሆኑት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አለማየሁ አቶምሳ ፣ በቅርቡ በተካሄደው ግምገማ ከስልጣን ሊነሱ ይችላሉ ተብሎ የተወራ ቢሆንም፣ ከፌደራል መንግስት በተሰጠ ትእዛዝ እንዳይተኩ ተደርጓል።

አቶ አለማየሁ በተሾሙ በወራት ውስጥ የግድያ ሙከራ የተደረገባቸው መሆኑ ይታወሳል። ቻይና ውስጥ ለወራት ሲታቀሙ ከቆዩ በሁዋላ በቅርቡ ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል። ይሁን እንጅ ህመሙ በስራ ቦታቸው ላይ እንዳይገኙ አድርጋቸዋል።

እርሳቸውን ለመተካት ያልተቻለው ለእርሳቸው የግድያ ሙከራ እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩት አፈጉባኤው አባ ዱላ ገምዳ በክልሉ ውስጥ ተመልሰው ተጽእኖ ይፈጥራሉ በሚል ምክንያት መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ።

አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ አሁን በተሰጣቸው ሀላፊነት ቦታ ደስተኛ አለመሆናቸውም ይነገራል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide