የእነ አቶ አንዱአለም አራጌ ቀጠሮ ሊራዘም ይችላል

የካቲት 24 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሽብርተኝነት የሀሰት ክስ ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት እነ አቶ አንዱአለም አራጌ ፣ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ብይን በመቃወም የመከላከያ መልሶቻቸውን ለማቅረብ ለፊታችን ሰኞ የካቲት 26፣ 2004 ዓም የተቀጠሩ ቢሆንም፣ ዳኞቹ የብይኑን ዝርዝር ለጠበቆች ማስተላለፍ ሲገባቸው እስካሁን ድረስ ለማስተላለፍ ባለመቻላቸው፣ ችሎቱ ለሌላ ጊዜ ሊራዘም እንሚችል ለማወቅ ተችሎአል።

ጠበቆቹ እስከ ትናንት ድረስ ብይኑ በጽሁፍ ተገልብጦ እንዳልተሰጣቸው ምንጮች ገልጠዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለማስፈታት የተቋቋመው ኮሚቴ ጋዜጠኛው በአስቸኳይ እንዲፈታ ጠይቋል።

ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንደር ነጋ የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚዎቹን ሁሉ ጸጥ ለማሰኘት የሚጠቀምበትን የጸረ  ሽብር አዋጅ በመንቀፍ ሲጽፍ እንደነበር አስታውሷል።

የኮሚቴው አስተባባሪ የሆኑት ጃሰን ማክለር የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በሀሰት ወንጀል ጥፋተኛ በማለት ለእስር የመዳረግ ልምድ እንዳላቸው ገልጠው፣ አንድን ጋዜጠኛ በሞት ፍርድ በሚያስቀጣ ወንጀል መክሰስ አረመኔነት ነው ብሏል። የአቶ መለስ መንግስት በጋዜጠኛው ላይ ያቀረበውን ክስ ሰርዞ ጋዜጠኛውን በአስቸኳይ እንዲፈታም እንዲሁም ምእራባዊያን በተለይ አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጠንካራ አቋም እንድትይዝ ማክለር ጠይቋል።

በአለማቀፉ የጋዜጠኞች ተንከባካቢ ድርጅት መሰረት በአሁኑ ጊዜ 7 ጋዜጠኞች በእስር ላይ ይገኛሉ። አገሪቱ በተሰደዱ ጋዜጠኞች ቁጥርም በአለም አንደኛ ናት።

የመለስ መንግስት የአረቡ አለም አብዮት መጀመሩን ተከትሎ የለውጥ ሀዋሪያ ይሆናሉ ብሎ የጠረጠራቸውን ሁሉ ወደ እስር ቤት መላኩ ይታወሳል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide