መለስ ዜናዊን በመቃወም በለንደን ታላቅ ሰልፍ እንደሚካሄድ ታወቀ

የካቲት 14 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-መለስ ዜናዊን የመሰለ አምባገነንና አሸባሪ ዘረኛ መሪ የሰላምና የመረጋጋት ዋስትና ሊሆን እንደማይችል ለአለም ህዝብ እናሳያለን! በሚል መሪ መፈክር ስር በተጠራዉ ታላቅ የተቃዉሞ ሰልፍ ላይ በለንደንና አካባቢዉ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዉያንና የሶማሊያ ተወላጆች እንደሚገኙ የሰልፉ አስተባባሪ ቡድን Net work against Repression & Injustice in Ethiopia ገልጿል።

በሶማሊያ ጉዳይ የብሪታኒያ መንግሰት ሐሙስ የካቲት 23 ቀን 2012 በጠራዉ አለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ለመገኘት የሚመጡት አቶ መለስ ዜናዊ ራበን ዳቦ ይሰጠን፣  ሰብአዊ መብቶች ይከበሩ፣ ብለው የጠየቁ ንጹህ  ዜጎችን፤ የፖለቲካ ተቃዋሚዎችንና ነፃ ጋዜጠኞችን በሽብርተኛነት የሃሰት ክስ በእስር በማሰቃየት ላይ የሚገኙ፤   በከተማም ሆነ በገጠር ዜጎችን ከነባር ይዞታቸዉ በተለያየ ምክንያት በመንቀል አገሪቷን ለባለሃብቶች በማቀራመት ተግባር ላይ የተሰማሩና በአፍሪቃ ቀንድ በየወቅቱ ስር እየሰደደ ለሚሄደዉ የሰላም እጦት በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ የሚሆኑ ግለሰብ በመሆናቸዉ በስብሰባዉ ላይ የመገኘት የሞራል ብቃት እንደሌላቸዉ አስተባባሪዎቹ ጠቅሰዋል።

ለአገሪቱ ዜጎች መብትም ሆነ ለአካባቢው ደንታ የሌላቸዉ፤ የአሸባሪ ዘረኛ አገዛዝ ቁንጮ መሆናቸዉን በጉባኤዉ ላይ ለሚሳተፉትና ለመላዉ አለም አቀፍ ህብረተሰብ እንደሚያሳዩ አስተባባሪዎቹ በበተኗቸዉ በራሪ ወረቀቶች አስታዉቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በለንደን ሶማሊያን በተመለከተ የሚካሄደዉ አለም አቀፍ ስብሰባ የሶማሊያ ተወላጆችን ፍላጎት ያላካተተ ነው ተብሎአል።

የፊታችን ሐሙስ የካቲት 23 ቀን 2012 የብሪታኒያ መንግሰት በለንደን ያዘጋጀዉ አለም አቀፍ ስብሰባ በፀጥታና በባህር ላይ ዉንብድና ላይ ከማተኮር ይልቅ በኢንቬስትሜንት፤ በስራ እድል፤ በፆታና በሰብአዊ ቀዉሶች ዙሪያ በሚያጠነጥኑ አጀንዳዎች ላይ እንዲያተኩር ሃሳብ በመሰንዘር ላይ በመሆኑ በሶማሊያና በዉጭ የሚገኙትን የሶማሊያ ተወላጆች ፍላጎት ላያካትት እንደሚችል ተገልጿል። 

ይህ የተገለፀዉ ግሎባል ዴቬሎፕሜንት የተሰኘዉ ድርጅት ባዘጋጀዉ የጠረጴዛ ዙሪያ ዉይይት ላይ ተሳታፊ የሆኑ የሶማሊያ ዜጎች በሰነዘሯቸዉ አስተያቶች ነዉ።

በዉይይቱ ላይ ተሳታፊ ከነበሩት መካከል ቀድሞ የሶማሊያ አምባሳደርና የአረብ ሊግ ረዳት ዋና ፀሀፊ የነበሩት መሃመድ ሸሪፍ መሃመድ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመሆን ሶማሊያን ለመደገፍ የሚሰራዉን ስራ እንዲመሩ ለ15 አገሮች በድብቅ የተበተነዉና በእጃቸዉ የገባ ሰነድ እጅግ እንዳሳሰባቸዉ ተናግረዋል።

 “የሽግግር መንግስቱ የተሰጠዉ ማንዴት እንዲያበቃና በምትኩ 15 አገሮች በአባልነት በሚገኙበት ኮሚቴ እንዲተካ የአለምአቀፉ ህብረተሰብ የያዘዉ እቅድ ቀጥተኛ ቅኝ አገዛዝ ነዉ።” በማለት ኢትዮጵያ ተቃራኒ የሆኑ የጦር አበጋዞችን ፍፃሜ በሌለዉ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ስፖንሰር ማድረጓን የቀድሞዉ ዲፕሎማት መሃመድ ሸሪፍ መሃመድ ከፍተኛ ነቀፌታ ሰንዝረዋል። 

የመንግስታቱን ድርጅት፤ የአለም ባንክን፤ ብሪታኒያን፤ ኢትዮጵያን፤ ኬንያንና ሌሎች አገሮችን ወደጋራ ስብሰባ ያመጣዉ አለም አቀፍ የሶማሊያ የግንኙነት ድጋፍ ሰጪ የተባለዉ ቡድን በስልጣን ላይ ያለዉ የሶማሊያ የሽግግር መንግሰት በገባዉ ስምምነት መሰረት ተግባሩን በመጪዉ ነሀሴ እንደሚጠናቀቅ በመግለፅ በሚያዝያ አጋማሽ አዲስ ህገ መንግሰት እንዲረቀቅ ጥሪ አቅርቧል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ ባንኪ ሙን እና  የአሜሪካን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪ ክሊንተንን ጨምሮ የ50 አገሮች ባለስልጣኖች፤ የአለም አቀፍ ድርጅቶችና የሶማሊያ የሽግግር መንግሰት ተወካዮች በስብሰባዉ ላይ እንደሚገኙ ይገመታል። 

በጠረጴዛ ዙሪያ ዉይይቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የሶማሊያ ተወላጆች እንደገለፁት ጉባኤዉ የሶማሊያ ህዝብን ፍላጎት የሚያራምድ አይሆንም፤ በአፍጋኒስታን ታሊባን እንደታየዉ ሁሉ በሶማሊያም አልሸባብ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ሊኖረዉ እንደሚገባ መጠቆማቸዉን ጋርዲያን ጋዜጣ አመልክቷል።

በሌላ ዜና ደግሞ የኢትዮጵያ ጦር ዛሬ የአልሸባብ  ዋና መናሀሪያ የሆነችውን ባይዶዋን ተቆጣትሯል።

ከ50 በላይ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና ከ20 በላይ ታንኮች በባይዶዋ መታየታቸውን የአይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጠዋል።

ኢትዮጵያ በአልሸባብ ላይ የሰነዘረችው ጥቃት እና አልሸባብ የስትራቴጄክ ከተማ የሆነችውን ባይዶዋን ለቆ መውጣት ነገ በሚከፈተው የለንደን ጉባኤ ላይ አቶ መለስ ዜናዊ ከፍተኛ ተሰሚነት እንዲኖራቸው ያደርጋል ተብሎአል። አቶ መለስም ጥቃቱ በአሁኑ ጊዜ እንዲሰነዘር ያደረጉት በጉባኤው ላይ ጠንካራ መሪ ሆኖ በመታየት የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት አስበው መሆኑን ይነገራል።

ኤርትራ በበኩሏ ሶማሊያን በተመለከተ የሚታየውን የውጭ ጣልቃ ገብነት አውግዛለች።

ኤርትራ ሶማሊያውያውያን የራሳቸውን ችግር እራሳቸው ይፍቱ የሚል አቋም አላት።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide