አንድነት ፓርቲ የአቶ አንዱአለም አራጌ ደህንነት አደጋ ላይ ወድቋል አለ

የካቲት 13 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዶ/ር ሀይሉ አርአያ፣ አቶ አስራት ጣሴ ፣ ኢ/ር ዘለቀ ረዲ እና አቶ ዳንኤል ተፈራ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኘው አቶ አንዱአለም አራጌ የካቲት 7 ቀን 2004 ዓም ከቀኑ 8 ሰአት ገደማ ለህይወቱ የሚያሰጋ ከባድ ድብደባ እንደተፈጸመበት ገልጠው፣ አቶ አንዱአለም በተፈጸመበት ድብደባ ምክንያት ከፍተኛ የአካልና የስነልቦና ጉዳት ደርሶበታል ብለዋል።

ለህይወቱ በመስጋት እስካሁን ድረስ ወደ ሆስፒታል ለመሄድ አለመፈለጉን ፣ ይሁን እንጅ ምርመራና የህክምና ርዳታ እንዲያገኝ ለማድረግ በቤተሰብ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጠዋል።

በህግ ጥላ ስር ያሉ ዜጎች በህይወታቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የሚከላከሉ ሀገራዊና አለማቀፋዊ ህጎች ቢኖሩም፣ የአቶ አንዱአለምን ደህንነት ከአደጋ ሊከላከሉት አልቻሉም ሲሉ አመራሮቹ ገልጠዋል።

በህገ መንግስቱ አንቀጽ 21 መሰረት በጥበቃ ስር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብአዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች መያዝ እንዳለባቸው መደንገጉን፣ እንዲሁም በወንጀል ህግ አንቀጽ 110(3) ላይ ውሳኔ ያላገኙ እስረኞች ውሳኔ ካገኙ ሌሎች እስረኞች ጋር አይቀላቀሉም የሚል ድንጋጌ ቢኖርም እነዚህና ሌሎች መብቶች ግን በአንዱአለም ላይ ተግባራዊ አልሆኑም ።

በአቶ አንዱአለም ላይ ድብደባ የፈጸመው እስረኛ ከእነ አንዱአለም ጋር ከነበረበት ክፍል ተወስዶ 300 ያህል ታራሚዎች ወደሚገኙበት ተዛውሮ ፣ በእስር ላይ ከሚገኘው ሌላው የአንድነት አመራር አባል ከሆነው ከአቶ ናትናኤል መኮንን ጎን እንዲተኛ ተደርጓል። እስረኛው በአቶ አንዱአለም ላይ የፈጸመውን አስነዋሪ ድርጊት በአቶ ናትናኤልም ላይ ሊፈጽም ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የፓርቲው አመራሮች ተናግረዋል።

በአቶ አንዱአለም ላይ የተፈጸመው በደል እንዲጣራና በበደል ፈጻሚው ግላሰብ ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ  እንዲሁም የማረሚያ ቤቱ አስተዳደርና መንግስት ህገመንግስቱንና አለማቀፍ ህጎችን በማክበር በህግ ጥበቃ ስር ላይ ለሚገኙ ዜጎች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እንዲያደርግ አንድነት ጠይቋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide