የካቲት 10 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ህወሀት ዛሬ በሚያከብረው 37 ኛ ዓመት በዓሉ ላይ፤ የቀድሞው የድርጅቱ ሊቀ-መንበር አቦይ ስብሀት ነጋ በቅርቡ በአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ቀርበው የአክሱም ታሪክ እንኳን ሌላውን ኢትዮጵያ፤ ከትግራይም አጋሜንና ተንቤንን አይመለከትም ማለታቸው፤ የድርጅቱ አቋም እንደሆነና እንዳልሆነ ግልፅ ያደርግ ዘንድ ፍትህ ጋዜጣ ጠየቀች።
ፍትህ ይህን ጥያቄ ያቀረበችው፤የድርጅቱን 37 ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በማስመልከት በህወሀት ዙሪያ አቋሟን ባንፀባረቀችበት መልዕክት ላይ ነው።
ከ1983ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ለተከሰቱ በጎም ሆነ መጥፎ ሁነቶችም በግንባር ቀደምነት ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው ህወሓት ነው ያለችው ፍትህ ፤ በአጠቃላይ ሲገመገም በሀገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ላይ የአንበሳውን ድርሻ የያዘው ህወሓት፤ ያበረከተው ጥቂት በጎ ነገር ቢኖርም እንደ ሀገር ሲታይ ግን ያጠፋው ይበዛል ብላለች።
ህወሓት የብሔር ጭቆና አለ ብሎ ብረት አንስቶ በሚታገልበት ዘመን፤ በወቅቱ ኢህዴን ይባል የነበረውና ዛሬ ብአዴን የሚል የአንድ ብሄር መጠሪያ የያዘው የብሔር ድርጅት እንዳልበረ ያስታወሰችው ፍትህ፤ ድርጅቱ ነፍጥ ያነሳውም አምባነንነትን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እቀይራለሁ ብሎ እንጂ ቀዳሚ የፖለቲካ ጥያቄው በኢትዮጵያ የብሔር ጭቆና አለ የሚል እምነት እንዳልነበር አውስታለች።
በደርግ ውድቀት ዋዜማ የተቋቋመው ኦህዴድም፤ በትጥቅ ትግሉ ላይ የነበረው ተሳትፎ እዚህ ግባ የሚባል ስላልነበረ፣ ደርግ ከወደቀ በኋላ በግንባሩ ውስጥ የተሰጠው ቦታ በትክክል ድርጅቱ ከወከለው ብሔር ህዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን እንዳይሆን አድርጐታል-ፍትህ እንዳለችው።
ደኢህዴን ደግሞ ጭራሽ በትግሉ ላይ ያልነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ የተቋቋመውም በ1985ዓ.ም መሆኑን ፍትህ አመልክታለች።
“በዚህ የተነሳ አራቱ ድርጅቶች በመሰረቱት ኢህአዴግ ውስጥ የህወሓት ሚና እና ተፅዕኖ ፍፁም የበዛ ሊሆን ችሎአል። ለዚህም ነው ፍትህ፤ የህወሓት ስህተቶች የመንግስት ስህተቶች ተደርገው ሊወሰዱ ይገባል የምትለው”ይላል ፍትህ ዛሬ የሚከበረውን 37ኛውን የህወሀት በዓል በማስመልከት ለድርጅቱ ባስተላለፈችው መልዕክት።
የኢትዮጵያ ታሪክ የ3000ሺ አመት ሳይሆን የ100 ነው የሚለው የታሪክ ብረዛ ምንጭም ህወሓት እንደሆነ፣ በተደጋጋሚ ጊዜ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ተቃርኖ ውስጥ በመግባት ‹‹ነፃ ላወጣው›› ተመሰረትኩለት ከሚለው ህዝብ አቋም እና ፍላጐት በእጅጉ ያፈነገጠ እና የራቀ የታሪክ አመለካከት ሲያንጸባርቅ የቆየና ከምስረታው ጀምሮ በሩን የዘጋ ወይም እጅግ ምስጢራዊ ከመሆኑ የተነሳ ለታሪክ ተመራማሪዎችም ሆነ ለጋዜጠኞች ዝግ የሆነ ድርጅት እንደሆነም ፍትህ አውስታለች።
“በቅርቡ የቀድሞ የህወሓት ሊቀመንበር አቦይ ስብሓት ነጋ በአሜሪካ ሬዲዮ ጣቢያ በሚተላለፈው የትግርኛ ፕሮግራም ላይ ቀርበው የአክሱም ታሪክ የኢትዮጵያ አይደለም፤ ከትግራይም የአጋሜ አውራጃን እና ተንቤንን አይመለከትም በሚል ያቀረቡት ትንተና ህወሓት ከታሪክ ጋር ያለውን ታሪካዊ ፀብ ሊያመላክት የሚችል በመሆኑ፤ በዚህ በምስረታ በአሉ ላይ ይህ አቋም የግለሰቡ ወይም የፓርቲው ለመሆኑ ይፋ ይሆን ዘንድ ፍትህ ትጠይቃለች!”በማለትም ጋዜጣዋ ጠይቃለች።
ከዚህ ባሻገርም ህወሓት በትግሉ ዘመን ያፈራሁት ነው በሚል በኤፈርት ስም ያቋቋመው የንግድ ድርጅት ገቢ እና ወጪው፣ ትርፉ እና በሀገሪቱ የንግድ ስርዓት ላይ እያደረሰ ያለው በጎም ይሁን መጥፎ ገፅታ ይፋ ሊሆን ይገባዋል”ያለችው ፍትህ፤ የኤፈርት ገቢ የት እንደገባ፣ ከኤፈርት በሚገኘው ትርፍ ምን እንደተሰራና ማን እንደተጠቀመም የመጠየቂያው ጊዜ አሁን ነው ብላለች።
ለሌሎችም ተያያዥነት ላላቸው ጉዳዮች ህወሀት በምስረታ በዓሉ ላይ ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፍትህ በርካታ ጥያቄዎችን አቅርባለች።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide