በኦሞ ሸለቆ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ህይወታቸው አሣሳቢ አደጋ ውስጥ ወድቋል ተባለ

የካቲት 10 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በታችኛው ኦሞ ሸለቆ  አካባቢ የሚኖሩ 200 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መሬታቸው ለህንድ ኩባንያዎች በመሰጠቱ ህይወታቸው አሣሳቢ አደጋ ውስጥ መውደቁን አልጀዚራ ዘገበ።

በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የ አካባቢው ነዋሪዎች  መሬታቸው “ለልማት ይፈለጋል”ተብለው በግዳጅ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ሲሆን፤ ቤታችንን እና ይዞታችንን አንለቅም ያሉ ደግሞ እየታሰሩ ነው።

በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት እነዚህ ዜጎች እየተፈናቀሉ ያሉት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በህንድ ኩባንያዎች ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ለሚታገዘውና “ኩራዝ የስኳር ልማት” ለተሰኘው ፕሮግራም እንዲውል በማለት በበአካባቢው 300ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት መስጠቱን በተከትሎ ነው።

እንደ አልጀዚራ ዘገባ፤መንግስት ለስኳር ልማት በማለት ለህንድ ባለሀብቶች የሰጠው  ሰፊ መሬት፤ 200 ሺህ የሚጠጉ የአካባቢው ከብት አርቢዎች መኖሪያ ነው።

ብዙዎቹ አርብቶ አደሮች ያዞታቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፤ በመከላከያ ሰራዊቱ አማካኝነት ወደ አካባቢው የሚያስገቡ በርካታ መንገዶች ተዘግተው – በግዳጅ እየተፈናቀሉ እንደሆነ የዜና አውታሩ ዘገባ ያመለክታል።

መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው የኦክላንድ ኢኒስቲቲዩት ባወጣው ሪፖርት ፤ የመከላከያ ሰራዊቱ በኦሞ ሸለቆ በሚገኙ ቦዲ፣ ሙርሲ እና ሱሪ በተባሉ መንደሮች በመስፈር ነዋሪዎቹ ስለ ስኳር ልማቱ ያላቸውን አመለካከት ለመቀየርና ተቃውሞውን ለማዳፈን ያደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ ፤በነዋሪዎቹ ላይ ግፍና እንግልት እንዳደረሰባቸው ገልጿል።

በተለይ የመፈናቀሉን ሀሳብ አምርረው የተቃወሙ በርካታ ነዋሪዎች በየእስር ቤቶቹ ከመወርወራቸውም ባሻገር፤ተቃውሞ ባሰሙት ሴቶች ላይ በሠራዊቱ አባላት የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደተፈጸመባቸው ሪፖርቱ አጋልጧል።

ለእርሻ ልማት እንዲውል ተብሎ ለህንድ ባለሀብቶች የተሰጠው የኦሞን ማጎ ብሔራዊ ፓርክ አብዛኛውን የኦሞ ሸለቆ የሚያካልል ሲሆን ፤ህይወታቸውን በሙሉ ከአካባቢው ጋር አቆራኝተው ሲኖሩ የነበሩት  በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮች ከመንግስት ወታደሮች ጋር ከመዋጋት ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው እየተናገሩ ነው።

በሰበአዊ መብቶች አከባበር ዙሪያ የሚሰራ አንድ የአካባቢው ሰው ለጋዜጠኞች እንደገለጸው ከሆነ “ብዙ ነዋሪዎች የሚኖሩት በፍርሀት ነው፤ ይሁንና አሁን የቀራቸው ነገር ስለሌለ- ተገደን ከምንፈናቀል  እስከመጨረሻው እንዋጋለን እያሉ ነው። ሁኔታው ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዳያመራ ስጋት አለን።” ብሏል።

አንድ የጎሳ አለቃ በበኩላቸው እንባ እየተናነቃቸው፦ “ሁሉንም ነገር ልናጣ ነው። የአደን ስፍራችን፣ የግጦሽ መሬታችንም ሆነ መኖሪያ ቤታችን እያለቀለት ነው። ያለአንዳች ነገር ባዶ እጃችንን  መቅረታችን ስለሆነ፤ የዓለማቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ  እንሻለን።” ሲሉ የድረሱልን ጥሪ ሲያቀርቡ ተሰምተዋል።

“ሰርቫይቫል ኢንተርናሽናል” የተባለው  ድርጅት በበኩሉ የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን በግዳጅ  ማፈናቀሉን እንዲያቆምና ዜጎችን በማፈናቀል ሊያካሂደው የወሰነውን የእርሻ እቅድ እንዲሰርዘው በአፅንኦት ጠይቋል።

ሊዝ ሀርተር የተባለችው የሰርቫይቫል ኢንተርናሺናል ሠራተኛ፦ “ ጎሳዎቹ ለከብቶቻቸው የሚያውሉት የግጦሽ መሬታቸው ሳይቀር ለመንግስትና ለውጭ ካምፓኒዎች ሊሰጥባቸው መሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል።” ብላለች።

በቅርቡ ለሳውዲት አረቢያና ለቻይና ሩዝ አምራቾች ሲባል 70ሺህ የሚሆኑ ዜጎች ከጋምቤላ አካባቢ በግዳጅ መፈናቀላቸው ይታወሳል።

ይህ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች የአገሪቷን ሰፋፊ መሬቶች እንዲቆጣጠሩ መደረጉ በመዲናወ በአዲስ አባባ ሳይቀር ህዝቡን እያሸበረው መሆኑን የአልጃዚራ ሪፖርት ያመለክታል።

“ይህ አዲስ አይነት ቅኝ አገዛዝ ነው።” የሚለው አንድ በአዲስ አበባ የሚኖር መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰራተኛ “ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የሀገሪቷ ሰፋፊ ግዛቶች በውጭ አገራት ኢንቨስተሮች እየተወሰዱ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ የት እንደምንገኝ ማሰቡ ያስፈራል።” ሲል ስጋቱን አሰምቷል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide