አንዳንድ ሙስሊሞች የማስፈራሪያ መልእክት እየደረሳቸው መሆኑን ለኢሳት ተናገሩ

የካቲት 10 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-አንዳንድ ሙስሊሞች የግንቦት7፣ የኤርትራ መንግስት፣ የአልሸባብና የአልቃይዳ ወኪሎች መሆናችሁ ተደርሶባችሁዋል  የሚል መልእክት እየደረሳቸው መሆኑን ለኢሳት ተናገሩ

ድምጻቸው ወይም ምስላቸው እንዳይወጣ የጠየቁት ሙስሊሞች በአወልያ መስጊድ ለተገኘው ዘጋቢያችን የደረሰባቸውን ማስፈራሪያና ዛቻ አጫውተውታል።

አንድ የ25 አመት ወጣት ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ባለፈው ሳምንት ከስግደት ሲመለስ፣ ” የምትሰራውን ደርሰንበታል፣ ከእነማን ጋር እንደምትገናኝ ዝርዝር መረጃ እጃችን ላይ አለ። እንቅስቃሴህን ባታቆም በአሸባሪነት ትከሰሳለህ። ” ብለው እንዳስፈራሩት ገልጧል።

በተመሳሳይ ማስፈራሪያ የደረሰው የፒያሳ ነዋሪ የሆነው ጎልማሳ፣ በአካባቢው የሚገኙ ፖሊሶች ጠርተው እንደናጋገሩት ገልጧል። ከተቃውሞው ጀርባ ግንቦት7 እና የኤርትራ መንግስት እጅ እንዳለበት ደርሰንበታል፤ የስልክ ልውውጦችም ተቀድተው ተይዘዋል። ሙስሊሙን ለመከፋፈልና ሰላምና ብጥብጥ ለማድረግ የምታደርገውን እንቅስቃሴ ባታቆም በህይወትህ እንመጣብሀለን ።” እንዳሉትና ከ4 ሰአት በላይ አግተውት እንደቆየ ተናግሯል።

ከአዲስ አበባና አቅራቢያ ከተሞች በአወሊያ መስኪድ የተሰባሰቡ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በጊዜያዊ ኮሚቴ አባልነት ከመረጧቸው 17 ተወካዮች ጋር በቀጣይ ማድረግ ስለሚገባቸው ተቃውሞ ትናንት ሲመካከሩ መዋላቸው ይታወሳል።

በአንፃሩ በአንዋር መስኪድና ፒያሳ በሚገኘው ኑር (በኒ) መስኪድ የዓርብ ጸሎት ለማድረስና ለመስገድ የተሰባሰቡት ምእመናን ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት (መጅሊስ) ስለ አህባሽ አስተምህሮ እያወደሱ ለማስተማር የሞከሩ የመጅሊስ ተወካዮች በምእመናኑ ከፍተኛ ተቃውሞ ከመስኪዶቹ እንዲወጡ ተደርጓል።

በአወሊያ መስኪድ በየሳምንቱ የዓርብ ጸሎት ላይ የሚደረገው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት (መጅሊስ) ይፍረስልን እና የኢህአዴግ መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ እየገባ የአህባሽን አስተምህሮ በግድ እንድንቀበል አያስገድደን የሚል ተቃውሞ ማድረግ ከጀመሩ ስምንተኛ ሣምንታቸውን የያዙ ሲሆን ቁጥራቸውም በየሳምንቱ እየተበራከተ በመቶ ሺህ ደረጃ ከፍ ብሏል፡፡

በትናንትናው እለት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ የአዲስ አበባና አካባቢው ሙስሊሞች ከዊንጌት ከፍ ብሎ በአስኮ መንገድ በሚገኘው አወሊያ መስኪድ ከማለዳ ጀምሮ በመሰባሰብ እስከ ቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ድረስ ሀዲስ በማድመጥ፣ በመስገድ እና በቀጣይ ማድረግ ስለሚገባቸው ሰላማዊ ትግል ላይ ተመካክረዋል፡፡

በህዝበ ሙስሊሙ በጊዜያዊ ተወካይነት ከመንግሥት ጋር እንዲነጋገሩ ከተመረጡት ውስጥ ሸህ አቡበከር አህመድ ለምእመኑ እንደተናገሩት የመንግሥት ሰዎች መፍትሄ ለመስጠት ለየካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም የቀጠሩን ስለሆነ እስከዚያው በሰላማዊ መንገድ እየታገልን እንቆያለን፤ ነገር ግን ከዚያ በኋላ መፍትሄ ካልሰጡን ጀማው ማድረግ የሚገባንን ይወስናል ብለዋል፡፡

አቶ አቡበክር “ከመንግሥት ቃል የተገባልን  እናንተ ሰላማዊ ሰዎች ናችሁ፣ ጥያቄዎቻችሁን ተቀብለናል፣ በቅርቡ መፍትሄ ታገኛላችሁ፣ ቢሉንም የመጅሊስ ሰዎች በየመስኪዱ የአህባሽን አስተምሮ አልቀበልም ያለውን ሙስሊም ሁሉ አልሸባብ፣ አልቃይዳ፣ የኤርትራና የኢሳያስ ተላላኪ፣ ሽብርተኛ እያሉ በመፈረጅ የሚለጥፉት ማስፈራሪያ አሁንም አልቆመም፡፡ ህዝበ ሙስሊሙን ለማስፈራራት ፖሊስ መስኪድ ውስጥ ድረስ ያስገባሉ” በማለት አክለዋል፡፡

በትናንትናው እለት  ተቃውሟቸውን ለመግለጽ ከአዲስ አበባ ብቻ መቶ አምሳ ሺህ የተቃውሞ ፊርማ  ተሰብስቧል፡፡ በቅርቡም በየክልሎቹ የሚገኙ ሙስሊሞች የፈረሙት ፊርማ ሲሰበሰብ ቁጥሩ እጅግ ከፍ ይላል በማለት ሪ‹ፖርተራችን ያናገራቸው አንድ የኮሚቴው አባል (ሥማቸውን ለመግለጽ አልፈቀዱም) አስረድተዋል፡፡

ከአንዋር መስኪድ የጁምዓ ጸሎት መልስ ሪፖርተራችን ያናገራቸው ኢማም መጅሊሱና መንግሥት የተሳሳተ ስሌት ውስጥ ገብተዋል፤ በዛሬው የዓርብ ጸሎት ወደ አወሊያ መስኪድ ያልሄዱትና በአንዋር መስኪድና ፒያሳ በሚገኘው በኑር መስኪድ የቀሩት ምዕመናን ሁሉ የእኛ ደጋፊዎች ናቸው በሚል የአህባሽን አስተምህሮ እያወደሱ ሊያስተምሩ በመመኮራቸው ምዕመኑ አላህ- ኡ ክበር እያለ በመቃወም ከመስኪዶቹ እንዲርቁ ተደርጓል ብለዋል፡፡

ይሄ ሁኔታም ባለፈው ቅዳሜና እሁድም በአንዋር እና በኑር መስኪዶች መጅሊሱና የመንግሥት ሰዎች የአህባሽን አስተምህሮ እያወደሱ ለማስተማር የሞከሩ ሲሆን ምዕመኑ ጠንክሮ በመቃወሙ ፖሊስ መጥቶ የመጅሊሱን ተወካይ ሸህ ጣሃ አሩን ድብደባ እንዳይደርስባቸው ከአንዋር መስኪድ አጅቦ አውጥቶ ሸኝቷቸዋል፡፡

ፒያሳ በሚገኘው ኑር መስኪድ በእለቱ የአህባሽን ትምህርት እንዲያስተምሩ የተመደቡት የወረዳው መጅሊስ አባል አቶ ላለምዶ ከምክትል ኢማሙ ሸህ ሰዒድ ጋር በተቃውሞ ተባረዋል፡፡

ትናንት በአወሊያ መስኪድ በተበተነው የተቃውሞ ወረቀት ላይ፡- የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ም/ቤት (መጅሊስ) አመራሮች በሙሉ የህዝበ ሙስሊም ውክልና የሌላቸው በመሆኑ በህዝበ ሙስሊሙ በሚመረጡ አመራሮች እንዲተኩልን፣ በመጅሊስ አማካኝነት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ እየተጫነ ያለው የአህባሽ አስተሳሰብ እንዲቆምልን፣ አወሊያ የህዝበ ሙስሊሙ ነፃ ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል መጅሊስ እጁን እንዲያነሳ፣ የመሪ ድርጅታችን አመራሮችን ለመተካት በምናደርገው ጥረት መንግሥት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግልን፣ እነዚህን ጥያቄዎቻችንን ከግብ ለማድረስ ከዚህ ቀጥሎ የተመለከቱትንን ግለሰቦች በኮሚቴነት የመረጥን መሆኑን በፊርማችን እናረጋግጣለን፡፡ ይላል። በኮሚቴነት የተመረጡት

  1. ሸህ መከተ ሞሄ (ከዑለማእ)
  2. ሼህ መሐመድ ከድር (ከዑለማእ)
  3. ሸህ ሱልጣን አማን(ዑለማእ)
  4. ሸህ ጣሂር አብዱልቃድር (ዑለማእ)
  5. ሐጂ አየነው ሙሐመድ (ከሽማግሌ)
  6. አቶ ዑመር አብዱልረዛቅ (ከምሁራን)
  7. ሸህ አብደላ ኢድሪስ (ከዑለማእ)
  8. ሸህ ዮሱፍ ሙዘሚል (ከሽማግሌ)
  9. ያሲን ኑሩ (ከዱዓት)
  10. አቡበከር አህመድ (ከዱዓት)
  11. ካሚል ሸምሱ (ከዱዓት)
  12.  አህመድ ሙስጠፋ (ከምሁራን)
  13. ጀማል ያሲን (ከዱዓት)
  14.  ረ/ት ፕሮፌሰር አደም ካሚል (ከምሁራን)
  15. ሐጂ ሁሴን ላለምዳ (ከሽማግሌ)
  16. ሀጂ ከማል ኑሪ (ከሽማግሌ)    ናቸው።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide