የካቲት 9 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ላለፉት ጥቂት ቀናት መረጋጋት የሰፈነበት ይመስል የነበረው የጋምቤላ ክልል ከትናንት ሁሙስ የካቲት ስምንት ቀን ከሰአት ጀምሮ በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሚገኝ ምንጮች ገልጠዋል።
ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላትና አንድ ሲቪል ሰራተኛ በላንድ ክሩዘር መኪና ከዋና ከተማዋ ጋምቤላ ተነስተው 70 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደ ሚገኘው የ አበቦ ወረዳ በማምራት ላይ ሳሉ ሁለት የፌደራል ፖሊስን የደንብ ልብስ የለበሱ ታጣቂዎች እንዲያቆሙ ሲጠይቋቸው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሁለቱ የፌደራል ፖሊስ አባላት ወዲያውኑ ሲገደሉ ሲቨል ሰራተኛው ደግሞ ቆስሎ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።
ታጣቂዎቹ የ ሟች ፖሊሶችን የጦር መሳሪያ ይዘው ወደ ጫካ ገብተውም ተሰውረዋል። ከጥቂት ሰአታት በሁዋላ አካባቢውን የተቆጣጠሩት የፌደራል ፖሊስ አባላት ገዳዮችን ለመያዝ ጥረት ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም።
በክልሉ የሚፈጸመው ግድያ መበራከት ያሰጋቸው የመንግስት ሰራተኞች፣ የሼክ ሙሀመድ አልአሙዲ ንብረት የሆነው የሳውዲ ስታር እርሻ ሰራተኞች እና የመንግስት ባለስልጣት ወታደራዊ አጀብ ካልተደረገልን መንቀሳቀስ አንችልም በማለታቸው በአካባቢው ያለው የስራ እንቅስቃሴ በእጅጉ ተዳክሟል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኦባንግ ኦሞት፣ ለአቶ መለስ ከሚደረገው ወታደራዊ ጥበቃ ባልተናነሰ ሁኔታ ታጅበው ዛሬ ወደ አዲስ አበባ በረዋል።
ሌሎች የክልሉ ባለስልጣናትም መከላከያ ሰራዊት ወም የፌደራል ፖሊስ አባላት ካላጀቡን በስተቀር ከዋና ከተማዋ መውጣት አንችልም የሚል አቤቱታ በማሰማታቸው፣ የፌደራሉ ፖሊስ አባላት ዋና ዋና የሚባሉትን ባለስልጣናት ለማጀብ እየተገደዱ ነው።
በአበቦ አካባቢ የሚገኙት ሰፋፊ የእርሻ ስራዎችን የሚሰሩት የሼክ ሙሀመድ አልአሙዲን ሳውዲ ስታርና የህንዱ ካራቱሬ ሰራተኞችም አስተማማኝ ሰላም እስኪሰፍን ድረስ ስራ እናቆማለን እያሉ ነው።
ሰራተኞች እንደሚሉት ጥቃቱን የሚፈጽሙት የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች መሆናቸው ግራ አጋብቶዋቸዋል። አንድ ሰራተኛ “ጥቃቱን የሚፈጽሙት አንድ አይነት ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች መሆናቸው ፣ እውነተኛ የፌደራል አባላትንና ታጣቂዎችን ለመለየት ፣ ተቸግረናል። ” ብሏል።
በቅርቡ የህወሀት የደህንነት ሰው የነበሩት አቶ ጌታቸው አንኮሬ ከተገደሉ በሁዋላ በአካባቢው ያለው ችግር እየተባባሰ ሄዷል
ጥቃቱን የሚፈጽሙት ሰዎች ማንነት እስካሁን በይፋ ባይነገርም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን በክልሉ የሚደረገውን የመሬት መቀራመት የሚቃወሙ ተወላጆች እና የመለስን አገዛዝ የሚቃወሙ በስልጣናት ናቸው ይላሉ።
አቶ ኦባንግ ኦሞት በቅርቡ በተደረገ ግምገማ የፓርቲያቸውን የመሪነት ቦታ ቢያስረክቡም አሁንም የክልሉ ፕሬዚዳንት ሆነው ቀጥለዋል። አቶ ኦሞት በግምገማው ወቅት እኔ በጋምቤላ ጭፍጨፋ የምጠየቅ ከሆነ ትእዛዙን የሰጠኝ መለስ ዜናዊም መጠየቅ አለበት ብለው መናገራቸው መዘገቡ ይታወሳል።