አወልያ መስጊድ ታህሪር አደባባይ ሆኖ መዋሉ ተዘገበ

የካቲት 9 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢሳት ዘጋቢ እንደገለጠው በዛሬው እለት በአወልያ መስጊድና በዙሪያው ባሉ ቦታዎች ከ100 ሺ ያላነሰ ህዝብ ተገኝቷል ከሙስሊሙ የተወከሉ ሰዎች ባለፈው ሰኞ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ያደረጉትን ውይይት ሪፖርት ለመስማማት ህዝቡ አሰፍስፎ ይጠብቅ ነበር፡፡
ተወካዮቹ የህዝቡን ስሜት በመረዳት የመንግስት ባለስልጣናት ጥያቄያቸውን እንደተቀበሉዋቸው እና የመጨረሻ መልስ ለመስጠት ለየካቲት 26 ቀነ ቀጠሮ እንደሰጧቸው ተናግረዋል።
በርካታ ወጣቶች ተወካዮች በሰጡት መልስ እርካታ ባይሰማቸውም ተወካዮቻቸውን በማክበር የካቲት 26ትን በትእግስት ለመጠበቅ ቃል ገብተዋል። ይሁን እንጅ እስከዚያ ድረስ በእየለተ አርቡ ( ጁማ) እየተሰባሰቡ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ወስነዋል።
የመንግስት ድጋፍ ያለው የኢትዮጵያ እስልምና ምክር ቤት ህዝቡ ወደ አወልያ እንዳይሄድ ለማድረግ ተመሳሳይ ስብሰባ የጠራ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል።
አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የእንቅስቃሴው አባል እንደተናገረው ” ምክር ቤቱ የእንቅስቃሴውን ሂደት ጥላሸት ለመቀባት በኤፍ ኤም አዲስ 98 ነጥብ አንድ ራዲዮ ከፍተኛ ቅስቀሳ አካሂዷል፡ሙስሊሙ ግን የምክር ቤቱን ማስፈራሪያና ውትወታ ባለመቀበል በዛሬው እለት በነቂስ ወጥቶ ተቃውሞውን አሰምቷል፤ ብሎአል።
በዛሬው ተቃውሞ ተደጋግሞ የተሰማው መፈክር ” ህገመንግስቱን የሚጥሱትንና ህገመንግስቱን የጣሱትን መደገፍ ህገመንግስቱን መጣስ ነው” የሚል ነበር። “በሀይማኖታችን አንደራደርም፣ ሁሉም የሚሞተው አንድ ጊዜ ነው፣ መንግስት ድምጻችንን ይስማ፣ መንግስት እስከ ሚሰማን ትግላችንን አናቆምም” የሚሉ መፈክሮችም ተደምጠዋል።
በተለይ አንድ ታዳጊ ወጣት ሙስሊሙ መብቱን ለማሰከበር አለመቻሉን በመግለጥ ያቀረበችው ግጥም፣ ተሰብሳቢውን ያስለቀሰ እንደነበር በስፍራው የተገኘው ዘጋቢያችን አክሎ ገልጧል።